ለኀዘን፡ መልብስ ያለብን፡ ነጭ፥ ወይስ ጥቁር ልብስ ነው?

እኛ፡ የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያውያን፡ የመጀመሪያው ትንሣኤ ሕይወት ባለዕድሎች ስለኾንን፡ ‘የትንሣኤ ብርሃን ልጆች!’ ነንና፡ ከደስታ በስተቀር፡ ኀዘን የለብንም። በሠርግ፥ ወይም፡ የደስታ በዓሎቻችንን በምናከብርባቸው ጊዜያት ብቻ ሳይኾን፡ ሕያዋን ወገኖቻችን፡ ከመካከላችን፡ በሥጋ ዕረፍት ሲያንቀላፉ፥ ነጭ ልብስን ለብሰን፡ በሓሤት ተመልተን የምንሸኛቸው፡ በዚህ ምክንያት ነው። ጌታ፡ ‘ሙታናቸውን ይቀብሩ ዘንድ፡ ሙታንን ተዉዋቸው!’ ያላቸው፡ ሌሎች፡ “ክርስቲያኖች ነን” ባዮች ግን፡ የሞቱ ወገኖቻቸውን፡ ጥቁር ልብስን ለብሰውና መራራ የኀዘን ልቅሶን በማድረግ ሲቀብሩዋቸው እናያለን።

በዚህ ሃይማኖታዊ መሠረት ላይ የታነጸውን፡ ማለትም፡ የሥጋዊ ሞት ኀዘንን፡ ወደትንሣኤ ሕይወት ደስታ የለወጠውን፡ ይህን መለኮታዊ ሥርዓታችንን፡ያቃወሰውን ባዕድ ልማድ፡ የግብፅ Orthodox ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፡ ወደአገራችን ገብተው፡ በሙታን ቀብር ጊዜ፡ ልቅሶ እንዲለቀስና ለመራራው ኀዘን፡ ጥቁር ልብስ እንዲለበስ የሚያደርገው ባህል እንዲጠናከር በማድረጋቸው፡ እነሆ፡ እስካኹን ድረስ፡ እውነተኛው የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊው ሥርዓታችን ተግዞና ባዕዱ ልማድ ሠልጥኖ ይታያል።

ከላይ እንደተገለጸው፡ በዚህ መሠረት፡ ሕያዋን ወገኖቻችን፡ከመካከላችን፡ በሥጋ ዕረፍት ሲያንቀላፉ፥ የተዋሕዶ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት በመከተል፡ ነጭ ያገር ልብስን እንለብሳለን። ማኅሌትንና ቅዳሴን የተመላ ጸሎት እናካኺዳለን። ይኽም፡ የደስታና የምስጋና እንጂ፡ የኀዘንና የለቅሶ አለመኾኑን እዚኽ ላይ ማውሳቱ አስፈላጊ ይኾናል።