ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት ነው?

ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ በኅዋ ሰሌዳዎቿና መድረኮቿ፡ በሌሎቹም፡ የመገናኛ መስመሮቿ አማካይነት፡ ለአንባብያን ባቀረበቻቸው፡ "ኢትዮጵያዊው፡ በማንነቱ ፍለጋ!"፥ "ኢትዮጵያ፡ የዓለሙ መፋረጃ!"፥ "ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት"፥ "አዳምና ሔዋን በኢትዮጵያ!"፥ እንዲሁም፡ “ምሥራች! ከእናት ኢትዮጵያ! ለኢትዮጵያ ልጆች፤ ስለኢትዮጵያዊነት"፥ ደግሞም፡ "Ethiopia: The Classic Case"፥ በተባሉት መጻሕፍቷ ውስጥ፡ ስለዚህ፡ ታላቅ ርእሰ ነገር፡ ዝርዝር ሓተታ፡ በሚበቃ ተሰጥቶበታል። እዚህም ላይ፡ ከዚያ መጽሓፋዊ ማብራርያ የተውጣጣ፡ የተጨመቀ አጠቃላይ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ረዥም ዕድሜ ባለውና ሕያው በኾነው፡ በኢትዮጵያ ትውፊት፡ ህልውናን አግኝተው፥ እውን ኾነውና በሰውነት ጎልተው የሚታዩ፥ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ፡ በክብር ተመዝግበው የሚነበቡ፥ እግዚአብሔር አምላክ፡ ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ፡ ከሰው ልጆች ጋር የተካየዳቸው፡ ሰባት ኪዳናት ይገኛሉ።

እነዚኽም ኪዳናት፡ከዚኽ እንደሚከተሉት የተዘረዘሩት ናቸው፦

፩ኛ. ኪዳነ አዳም - በአዳምና ሔዋን ሥርዓተ ጋብቻ ምልክትነት የሚታወቀው።

፪ኛ. ኪዳነ ኖኀ - በቀስተ ደመና ምልክትነት የሚታወቀው።

፫ኛ. ኪዳነ መልከ ጼዴቅ - በኅብስትና ጽዋ ቁርባን ምልክትነት የሚታወቀው።

፬ኛ. ኪዳነ አብርሃም - በግርዛት ምልክትነት የሚታወቀው።

፭ኛ. ኪዳነ ሙሴ - በጽላትና ታቦት ምልክትነት የሚታወቀው።

፮ኛ. ኪዳነ ዳዊት - በዘውድ ምልክትነት የሚታወቀው።

፯ኛ. ኪዳነ ምሕረት - ከላይ የተጠቀሱት፡ የቀደሙት ስድስቱ ኪዳናት ታድሰው የተዋሃዱበትና ለዘለዓለም ጸንተው የሚኖሩበት፡ ሰባተኛውና የመጨረሻው፡ ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፡ በተሰቀለበት ሥጋውና ባፈሰሰው ደሙ ምልክትነት፡ የተገለጸውና የሚታወቀው ነው።

እነዚህ ኪዳናት፡ የየቅል መታወቂያቸው፡ ከላይ እንደሠፈረው፡ እውን በኾኑ፡ የተለያዩ ምልክቶች የተገለጹ ሲኾን፡ በሰውነት ገዝፈው የታዩት ደግሞ፡ ለፈጣሪያቸው ባላቸው እውነትና ፍቅር፡ እርሱን አምላካቸውን ባስደሰቱ ትሑታን ግለሰቦች ሕያው አካል ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ህልውናና የኢትዮጵያዊ ወይም የኢትዮጵያዊት ሕይወት፡ ኹለቱም፡ በእነዚህ በሰባቱ ቅዱሳት ኪዳናት ላይ በጽኑ ተመሥርተው፡ በተዋህዶ የተሣሠሩ ናቸው። ይህንንም፡ ከእነዚሁ ኪዳናት መንጭተውና በእነዚሁ ኪዳናት ለምልመው የሚታዩት፡ የኢትዮጵያውያን፡ የሃይማኖት፥ የባህልና የማኀበራዊ ኑሮ ሕይወታቸው ድርና ማግ ብቻ ሳይኾን፡ በትምህርት አሰጣጥ፥ በሀብት ልማትና በሥነ መንግሥት አመራር ረገድ፡ በሥርዓት የሚከተሏቸው፡ ሕያዋን የኾኑት አምላካውያት ሕጎቻቸው ጭምር፡ በገሃድ አረጋግጠው ያሳያሉ።

ኢትዮጵያዊነት፡ የመጠቀና የጠለቀ፥ የሰፋም ባሕርይ አለው፤ ይኸውም፡ ለኢትዮጵያ፥ እንዲሁም፡ ላለፉትና ለዛሬዎቹ፥ ለወደፊቶቹም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብቻ፡ ተለይቶና ተወስኖ የተሰጠ፥ እየተሰጠ ያለና የሚሰጥም አለመኾኑ ነው፤ ነገር ግን፡ በዘመነ ሓዲስ ኪዳን፡ ሞክሼው (መሰሉ) እንደኾነው፡ እንደክርስቲያንነት ኹሉ፡ የሰው ዘር፡ በመላ ተጠቃልሎ፡ በመለኮታዊቷ መንግሥት ሥር ተዋሕዶ፡ አንድ እንዲኾንበት፡ እግዚአብሔር አምላክ፡ ለፍጥረተ-ዓለሙ ደኅንነትና መልካም ሕይወት፡ አዘጋጅቶ የዘረጋው፡ ዘለዓለማዊ ዕቅድ ነው እንጂ። ይህም፡ በምድር ላይ ላለው፡ ለሰው ልጆች ችግር ኹሉ፡ የመጨረሻው መፍትሔ እንደሚኾን ይታመናል።

ወደ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ለመመለስ ይኽን ይጫኑት