ግብፃውያን፡ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙት በደል ምንድን ነው? ምክንያታቸውስ?

የሃይማኖት ወገኖቻችን በኾኑት፡ በባዕዳን አብያተ ክርስቲያናት፡ በተለይም፡ በግብፅ ቤተ ክርስቲያን የተጽዕኖ ኃይል ሠርገው ገብተው፡ መሠረት ከያዙትና እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያውያን የእምነት ባህል ላይ ሰፍነው ከሚታዩት፡ ረቂቃን ደባዎች መካከል፡ ጥቂቱን፡ እስቲ፡ አልፎ አልፎ፡ ከዚኽ እንደሚከተለው እንመልከት!

፩ኛ. “የአዳምና ሔዋን ልሳን” ተብሎ፡ ለዓለም ቋንቋዎች፡ ሥርና ግንድ ለኾነው ለ“ግዕዝ” ማንነት፡ መታወቂያው የኾነውንና በአሌፋቱ (በፊደሎቹ) ተራ፡ በግልጽ የሚታወቀውን፡ የ“አ(ኧ)በገደ”ን ሥርዓተ ፊደል፡ ግብፃውያን፡ ኾን ብለው፡ መሠረታዊ አቋሙን አፋልሰው፡ ደብዛውን ጭምር ለማጥፋት ሲሉ፡ ሥርዓቱን፡ ወደ“ሀሁ” ለውጠዋል።

፪ኛ. “ኢትዮጵያውያን፡ ከራሳቸው ወገኖች መካከል፡ ጳጳሳት እንዳይመርጡ፡ እንኳንስ መምረጥ፡ ግብፃውያን እንኳ፡ በእጩነት ለማቅረብ፡ የተካፋይነት መብት እንዳይኖራቸው፡ በኒቅያ ጉባዔ ተወስኗል፡” ብለው፡ ግብፃውያን፡ “ፍትሓ ነነገሥት” በተባለው መጽሓፋቸው፡ በሥርዋፅ (በእመጫት) በአዋጅ በማስታወቅ፡ ለ፩ሺ፮፻ ዓመታት ያህል አግደዋል።

፫ኛ. በኢትዮጵያውያን ዘንድ “ሰባቱ ኪዳናት” ተብለው የሚታወቁትና የቅዱሱ ኪዳን አካላት የኾኑት፡ የኢትዮጵያዊነት ተዋህዶ ሃያማነኖታችን መሠረቶች፡ መደበኛ ስማቸውና መለያ ምልክታቸው ተለይቶና ተዘርዝሮ ይገኛል። እነዚህም፡ “ኪዳነ አዳምና ሔዋን፥ ኪዳነ ኖኅ፥ ኪዳነ መልከ ጼዴቅ፥ ኪዳነ አብርሃም፥ ኪዳነ ሙሴና ኪዳነ ዳዊት፥ በመጨረሻም፡ በድንግል ማርያምና በኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘው ኪዳነ ምሕረት” የሚባሉት ናቸው። እነርሱ ግን፡ የእኒህን ሕያዋንና አምላካውያት ሀብታት ማንነትና ምንነት በመሠረዝ፡ በእነርሱ ቦታ፡ “ትምህርተ ኅቡዓት፥ ዘጠኙ፡ የሌሊት፥ የነግህና የሠርክ ኪዳናት፥ እግዚአብሔር ዘብርሃናት፥ በእንተ ቅድሳት፥ በሰማይ የሀሉ ልብክሙ እና ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ሥሉስ” የተባሉትን ጸሎታት መተካታቸው ነው።

፬ኛ. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስንና የቅድስት እናቱን፡ የድንግል ማርያምን፡ የልደታት ቀን፡ በትክክል ከሚውልበትና በመለኮት ዕፁብ ድንቅ፡ የሥነ ፍጥረት ሥራዎች ካሸበረቀው፥ በአምልኮተ እግዚአብሔር በዓላትም ከሠመረው፡ ከኢትዮጵያውያኑ መስከረም ፩ (አንድ) ቀን ገንጥለው ወስደው፡ በጣዖት አምልኮና በሰው ልጆች ሥረዓት ወደተወሳሰበው ወደፈረንጆቹ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን እንዲቀየር ያደረጉበት፡ ሰይጣናዊ ግብራቸው ነው።

፭ኛ. ለእናታችንና ንግሥታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፡ የቅዱስ ቁርባን ምስጋና ኾና፡ መሥዋዕት ሲቀርብባት የኖረቸው፡ “መዓዛ ቅዳሴ” የተባለች፡ ኢትዮጵያዊው፡ አባ ጊዮርጊስ፡ ዘጋስጫ የደረሱት፡ የቅዳሴ መጽሓፍ አለች። ይህች የቅዳሴ መጽሓፍ፡ “ከግብፃውያን የተገኙ” ተብለው ከሚታሰቡት፡ ከሌሎቹ፡ የቅዳሴ መጻሕፍቶቻችን መካከል፡ የኋላ ኃላ፡ በተለይ፡ አጼ ኃይለ ሥላሴ፡ የሥልጣን ዘመን፡ በግብፃውያኑ ጳጳሳት፡ ተለይታ እንድትወጣ፡ በእርሷ የመቀደሱ ባህልና ሥርዓትም፡ በመላ የኢትዮጵያ አድባራትና ገዳማት፡ እንዲቋረጥ አድርገዋል።

ቅዳሴ ማርያምና መዓዛ ቅዳሴ፡ ኹለቱም ቅዳሴያት፡ ከተደረሱበት ዘመን ጀምሮ፡ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን እስከተከሠተው፡ “የኅዳር በሽታ” ድረስ፡ በፍልሰታ ሱባዔ፡ ቅዳሴ ማርያም፡ በወርኀ ጽጌ ደግሞ፡ መዓዛ ቅዳሴ፡ በተለይም፡ መቅሠፍት በሚኾንበት ወራት፡ ማለትም፡ ቸነፈር (ወረርሽኝ በሽታ)፡ ድርቅና ረሃብ፡ ወይም ጦርነት በተነሣ ጊዜ፡ አብያተ ክርስቲያናት፡ ምሕላ እንዲይዙ ሲታዘዙ፡ “ምሕላ ያዙ! መዓዛ ቅዳሴን ቀድሱ!” እየተባለ፡ የምሕላው ጊዜ እስኪፈጸም ድረስ፡ መደዳውን የምትቀደሰው፡ መዓዛ ቅዳሴ ነበረች።

ግብፃውያን፡ የአገራቸው ሊቃውንት የደረሷቸውን የቅዳሴ መጻሕፍት ተቀብለውና አክብረው፡ በየትምህርት ቤቶቻቸው ሲያስተምሯቸውና በየቤተ መቅደሶቻቸው ሲቀድሱባቸው፥ በሌላውም አገር፡ አሠራጭተው እንዲሠራባቸው ሲያደርጉ፥ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አንኳ ሳትቀር፡ መዓዛ ቅዳሴን፡ ተቀብላና አክብራ፥ ከሊቃውንቱ ቅዳሴያትም፡ ቅድሚያ ሰጥታና ተራ አስገብታ በማሳተም፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን፡ በሮም ባሉ ቤተ መቅደሶቿ ጭምር እንድትቀድስ ስታደርግ፡ በግብፃውያን አመራር ሥር የነበረችው፡ የራሳችን ቤተ ክህነት፡ ከቅዳሴው መጽሓፍ አውጥታና ራሳቸው፡ ኢትዮጵያውያን እንዳይቀድሱባት ወስና፡ ወደውጪ መጣሏ፥ ይልቁንም፡ ነፃ የወጣችው፡ የዛሬዋ ቤተ ክህነት ኢትዮጵያውያን መሪዎች፡ ወደነበረችበት የክብር ቦታዋ ሳይመልሷት መቆየታቸው፡ እጅግ አስደናቂ ይኾናል።

በተለይም፡ የዚህ ኹሉ በደል፡ ምንጩ ምክንያት፡ መዓዛ ቅዳሴን የደረሳት፡ ኢትዮጵያዊ ሊቅ መኾኑና በጸሎቱ ውስጥ፡ የኢትዮጵያውያን አባት፡ የመልከ ጼዴቅ ስም መነሣቱ ሲኾን፡ እንደወንጀል ተቆጥሮ፡ የቅዳሴዋን ዕድል፡ ከዚኽ ማድረሱ፡ በጣሙን ያስቆጫል። ያሳዝናልም።

፮ኛ. በረቡዕ የውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፡ “አንቲ ዘበአማን ደመና፡ እነንተ አስተርአይኪ ለነ ማየ ዝናም”፡ “የዝናም ውኃን ቋጥረሽ የታየሽልን፡ እውነተኛ ደመና አንቺ ነሽ!...አንድም፡ ደመና ኖኅ አንቺ ነሽ!” ካለ በኃላ፡ ስለኖኅ መተረክ ሲጀምር፡ “እሠይም ቀስትየ በውስተ ደመናት፡ ከመ ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማየ አይኅ!” የሚለውን የመጽሓፍ ቃል ያቀርባል።

የዚኽ ቃል ቀጥተኛ ትርጉም፡ “ዳግመኛ፡ ምድርን፡ በጥፋት ውኃ የማላማስናት (የማላጠፋት) መኾኔን አስታውቅ ዘንድ፡ ቀስቴን በደመና አሳያለሁ!” ማለት ሲኾን፥ ጐልተው የሚታዩት የቀስተ ደመናው ዓበይት ቀለማት ደግሞ፡ ሦስቱ፡ ማለትም፡ አረንጓዴ፥ ብጫና ቀይ ሲኾኑ፡ የውዳሴ ማርያሙ፡ የአንደምታ ትርጓሜ ግን፡ በቅዱሳት መጽሓፍት ውስጥ የሌለውን፡ ከዚህ የሚከተለውን፡ ትርጉምና ሓተታ ሰጥቶ፡ ሲያብራራ እናገኘዋለን። ትርጉሙና ሓተታው እንዲህ ይላል፦ “ደመና በዞረ ጊዜ፡ ዐራት ኅብር አድርጌ፡ ቀርጬ አሳይሃለሁ፤ ይኽውም፡ ነጭ፥ ቀይ፥ ብጫ፥ ጥቁር ነው።” በማለት፡ ስለአራቱ ቀለማት ምሥጢር መግለጡን ይቀጥላል።

እንዲህ፡ ዓለሙ ጭምር በተቀበለው፡ በራሷ የኢትዮጵያ ቅዱሳት መጻሓፍት ውስጥ ተመዝግቦ ለሚገኘው፡ ለእውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል፡ ፈጽሞ የሌለና የተሳሳተ ትርጉም በመስጠት፥ ደግሞም፡ መላው ፍጥረት ዓለም፡ አረንጓዴ፥ ብጫና ቀይ ኾኖ፡ በጉልህና በገሃድ የሚያየውን የቀስተ ደመናውን ኅብር ቀለማት፡ በጥቁርና በነጭ ለውጠዋል። ኢትዮጵያና እውነተኞች ልጆቿ ኢትዮጵያውያን፡ ከፈጣሪያቸው ጋር፡ በቅዱሱ ኪዳን የተሣሠሩበትን፡ ከሰባቱ ኪዳናት፡ አንዱ ምልክታቸውና የማኅተማቸው አንዱ ክፍል የኾነውን፡ ሰንደቅ ዓላማቸውን፡ የሃይማኖት ደብዛው ሳይቀር ፈጽሞ ለማጥፋት መኾኑ ሊታበል አይቻልም።

፯ኛ. “ኢትዮጵያውያንን፡ ክርስቲያን ያደረግናቸው፥ ቤተ ክርስቲያናቸውንም መሥርተን ያቋቋምንላቸው፡ ወደኢትዮጵያ በገባንበት፡ በአራተኛው ምዕተ ዓመተ ምሕረት፡ እኛ ነን!” የሚለው የሓሰት ብሂላቸው ነው።

(ግብፃውያን፤ በኢትዮጵያውያን ላይ ያካኼዱትንና የሚያካኼዱትን፡ ግልጽ የማጥቃት ሥራ በበለጠ ለመረዳት፡ ኢትዮጵያ፡ የዓለሙ መፋረጃ! ከገጽ ፩፻፳፮ ጀምሮ፡ እንዲኹም፡ “ምሥራች” ከገጽ ፩፻፱፭ ጀምሮ ይመልከቱ።)