በፌስ ቡክ የኅዋ መድረካችን፡ ከአቶ ዞሚ ስንቱ የቀረበ ጥያቄና ለዚያ ጥያቄ የሰጠነው ምላሽ።

በፌስ ቡክ የኅዋ መድረካችን፡ ከአቶ "ዞሚ ስንቱ" ለቀረበልን ጥያቄ፡ በዚያው የኅዋ መድረክ፡ የሰጠነውን መንፈስ ቅዱሳዊ ምላሽ፡ ለእናንተ፡ የኅዋ ሰሌዳ አንባቢዎቻችንና ተከታታዮቻችን፡ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋልና በተለመደው የጥሞና መንፈስ ኹናችሁ ተከተታተሉት።

ከአቶ ዞሚ ስንቱ የቀረበ ጥያቄ፦

    ቃለ ሕይወት ያሰማልን! በመቀጠልም፡ ኹለት ጥያቄዎች አሉኝ።
    ፩. "በዚህም እውነታ፡ "ድንግል ማርያም፡ ከፍጥረተ ዓለሙ አስቀድሞ፡ በቅድስት ሥላሴነቷ፡ የሦስቱም አንድነት መገኛ እንደነበረች ኹሉ፡..." ሲል፡ ምን ማለት ነው? አልገባኝም።
    ፪. ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ከድንግል የተፀነሰው፡ ታኅሣሥ ፩ ከኾነ፥ ልደቱ፡ ከ፱ ወር በላይ አልፎ፡ እንዴት ታኅሣሥ ፳፱ ሊኾን ቻለ? በዚህ አቈጣጠር፡ ፲፪ ወር ከ፳፱ ቀን አይኾንም? እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

ከኢእመ የተሰጠ ምላሽ፦ 

    አንደኛ፤ የ''ቅድስት ሥላሴ''ን ምንነትና ማንነት፡ በእውነትና በመንፈስ ቅዱስ፥ ማለትም፡ በእግዚአብሔር እውነትና በመንፈስ ቅዱሳዊ አእምሮ ኾነው ካልተረዱት በቀር፡ በሰው መምህርነትና በሥጋዊ አእምሮ አስተዋይነት አይገለጽም። አዎን! በእውነትም፡ ይህ ምሥጢር፡ ለሥጋዊ አእምሮ ይጸንበታል! ይርቅበታል! ይረቅበታል! ይሠወርበታል! በመንፈስ ቅዱሳዊ አእምሮ ግን፡ ይህን፡ የራቀውን አቅርቦ፥ የረቀቀውን አግዝፎና የተሠወረውን ገልጦ ማየትና መመልከት ይቻላል። 
    ይህውም፡ "ድንግል ማርያም፡ ከፍጥረተ ዓለሙ አስቀድሞ፡ በቅድስት ሥላሴነቷ፡ የሦስቱም አንድነት መገኛ ነበረች" ማለት፡ ድንግል ማርያም፡ እምቅድመ ዓለም፡ "እግዚአብሔር" በሚለው፡ በፈጣሪ የአንድነት ህልውናና ስም ውስጥ፡ በሕያውነት ተገኝታ፥ ኋላም፡ በእግዚአብሔር አብ አባትነትና በእርሷ፡ በእግዚአብሔር እም እናትነቷ፡ እግዚአብሔር ወልድን፡ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ግብር፡ በመለኮትነት ስትወልደው፡ የሦስቱም፡ ''የአብ፥ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ''፡ አንዲት፡ መገለጫ አካል፡ ማለትም፡ "ቅድስት ሥላሴ" ለመኾኗ፡ እውነተኛ ምስክርና ማረጋገጫ ኾኗል። 
    ኋላም፡ በዚያው፡ በእግዚአብሔር አብ አባትነትና በእርሷ እግዚአብሔር እም እናትነቷ፡ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ግብር፡ በሰውነት፡ እግዚአብሔር ወልድን ስትወልድ፡ የሦስቱም፡ ''የአብ፥ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ''፡ አንዲት፡ መገለጫ አካል፡ ማለትም፡ "ቅድስት ሥላሴ" መኾኗ፡ በአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል፡ የአዋጅ ቃል፡ ለፍጥረተ ዓለሙ፡ ገሃድና ይፋ ወጥቷል።
    ይህ፡ ሕፃናት፡ በሩካቤ ሥጋ፡ ከአባት አብራክ ተከፍለው፥ በእናታቸው ማሕፀን ውስጥ ሲፀነሱ፡ እናትየው፡ የሦስቱም፡ "የግብሩ፥ የዘሩና የሕፃኑ"፥ እንዲሁም፡ የፅንሱ፡ "ሥጋዊ፥ ነፍሳዊና መንፈሳዊ አካላትና ባሕርያት፡" አንዲት መገለጫ አካል እንደኾነች ማለት ነው። 
    ኹለተኛ፤ እግዚአብሔር ወልድ፡ በሰውነት፡ የተወለደባት አማናዊት ዕለት፡ ''መስከረም አንድ'' ቀን ናት። ይህን እግዚአብሔራዊና ኢትዮጵያዊ እውነታ እስካኹን ሳያውቁ የቆዩ መኾንዎ፡ ለኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት የእውቀት ገበታ፡ ገና አዲስ እንግዳ መኾንዎን፡ በራስዎ ምስክርነት አረጋግጠዋል።
    እንዲህ ከኾነ፡ "ምናልባት፡ ሌሎች፡ አያሌ ጥያቄዎች ሊኖርዎት ይችላሉ!" ብለን መገመት ስለሚኖርብን፡ እነዚያን ጥያቄዎች ሊያቀርቡልን ከማሰብዎ በፊት፡ በዚህ በፌስቡክ ኅዋ መድረካችንና የመገናኛው አድራሻ ፡ ከዚህ በታች በተገለጸው፡ የኅዋ ሰሌዳችን ላይ የሠፈሩትን መልእክቶቻችንን፥ የተዘረዘሩትንም መጻሕፍቶቻችንን፡ አስቀድመው፡ በማስተዋል እንዲመለከቷቸው እንጋብዝዎታለን።