ለተደረገልን፡ አንድ በጎ ተግባር፡ በብዙኋኑ ዘንድ፡ ተቀባይነት ያገኘውንና የተለመደውን፡ ‘አመሰግናለሁ!’ የሚለውን ቃል መጠቀም፡ ተገቢ አለመኾኑ ለምን ነው? ከዚኽ የተሻለ ሌላስ፡ ምን ሊኖር ይችላል?

ምስጋና የሚቀርበው፣ የሚገባውም፡ ለሰው ሳይኾን፡ ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። ለሰው፡ በሚያስፈልግበትና ደግሞም፡ አግባብ በሚኾንበት ጊዜ፡ የሚመለስለት አጸፋ፡ ‘እግዚአብሔር ይመስገን! እግዚአብሔር ይስጥልኝ! ዋጋህን፥ ዋጋሽን፥ ዋጋውን፥ ዋጋችሁን፡ እግዚአብሔር ይክፈልልኝ! ይባርክህ! ይባርክሽ! ይባርካችሁ!’ ወይም፡ እንደነገሩ ኹኔታ፡ የሚስሰጠው የማበረታች ቃል፡ ‘ጎሽ! መልካም! በርታ! በርቺ! በርቱ!’ የሚለውን የመሰለ ሊኾን ይገባል።

በዚህ ረገድ፡ መምህራችን፣ ‘እናንተ፡ ያዘዝኋችሁን ኹሉ አድርጋችሁ፡ ‘ምንም ያልሠራን አገልጋዮች ነን፤ ያደረግነውም፡ የሚገባንን ነው፤’ በሉ!’ ሲል፡ የሰጠን መሪ ቃል ይታወሳል። ማቴ. ምዕ. ፮፣ ቁ. ፯-፲፭፣፴-፴፫፤

ለሰው፡ ምስጋና አይገባውም! የሚባለው፡ ስለኹለት ምክንያቶች ነው፤

፩ኛ. ሰው የተፈጠረው፡ በጎ ለማድረግና የሚጠበቅበትም በጎ ሥራ ብቻ ስለኾነ፣ የተፈጥሮ ግዳጁ በኾነው፡ በዚኽ አቋሙ፡ በማናቸውም ቦታ፣ ጊዜና ኹኔታ፡ ለማናቸውም ፍጡር፡ በሚፈጽመው በጎ ተግባር፡ ‘የሚገባውን አደረገ!’ ሊባል እንጂ፡ ከዚኽ ያለፈ ምስጋና ሊቀርብለት አይገባም። አንድ ሰው፡ ከተለመደው በጎ ሥራ፡ የተለየ፡ ተቃራኒ ድርጊት የፈጸመ እንደኾነ፣ ‘አጠፋ!’ የሚባለው፣ ሰው፡ የተፈጠረው፡ ለበጎ ሥራ ብቻ መኾኑን ማመልከቱ አይደለምን?

፪ኛ. አንድ ሰው፡ ዛሬ፡ ‘የሚያስመሰግነው ነው!’ የሚባለውን ሥራ ሠርቶ ቢመሠገን፣ ጥቂት ቆይቶ ደግሞ፡ የሚነቀፍበት፡ አንድ ሌላ ሥራ ሲፈጽም ይገኛል፣ ስለዚህ፡ ትናንት ያመሰገነው ሰውዬ፣ ዛሬ ደግሞ፡ ያው ሰውዬ መልሶ፡ ሲነቅፈው ይሰማል፤ ‘ባንድ ራስ፡ ኹለት መላስ!’ ማለት ነው። እንዲሁም፡ ያንዱን ሰው ሥራ፡ አንዱ፣ ሥራውንም፥ ሠሪውንም ሲያመሰግን፣ ሌላው ግን ይነቅፈዋል። ከዚኽም ሲያልፍ፣ በሕይወት ሥጋ ሣለ የተመሰገነ አንድ ሰው፣ ከሞተ በኋላ፡ ሲነቀፍ፣ በሕይወት ሥጋ ሣለ፡ የተነቀፈ፣ ከሞቱ በኋላ፡ ሲመሰገን ይስሰማል።

ይኽ ኹሉ የሚያሳየው፡ ለፍጡር፡ የሰው ምስጋና፡ የባሕርይ ገንዘቡ አለመኾኑን ነው፤ ምስጋና የሚገባው እንኳ ቢኾን፣ ይኽንኑ የሚያገኘው፡ እውነተኛውን ተመስጋኝ ከሚያውቀው፣ የመጨረሻውንም ፍርድና ዋጋ ለእያንዳንዱ ከሚሰጠው፣ እርሱ ብቻ፡ ፈጣሪና የምስጋና ባለቤት ከኾነው፡ ከእግዚአብሔር ነው።

‘ምስጋና የሚገባው፡ እግዘኢብሔር ብቻ ነው!’ የሚባለውም፡ በብዙ ምክንያቶች መነሻነት ነው። ሰውን ኾነ፥ ሌላውን ፍጥረቱን፡ እንዲህ አከናውኖ በመፍጠሩ፣ እንዲሁም፡ ከማያልቅ ምንጩ ስለሚመግበውና በሕይወት ስለሚያኖረው፡ ፈጣሪ እግዚአብሔር፡ በሥነ ፍጥረቱ አማካይነት ይመሰገናል። ሳይለመንና ሳይጠየቅ፡ አስቀድሞ፡ ለፍጥረቱ ኹሉ ያደረገውና የሚያደርገው፡ የጸጋ ስጦታውና በረከቱ፡ ፍጹምና እጅግ የተትረፈረፈ፣ ወሰን የሌለውም ስለኾነ፡ እግዚአብሔርን፡ ፍጥረቱ ኹሉ ያመሰግነዋል። ይልቁንም፡ የሰው ልጅ፡ የዘለዓለም ሕይወት ባለቤት እንዲኾን፡ በየዘመናቱ ባደረገለት ምሕረት፣ ቸርነትና ቤዛነት፡ እግዚአብሔር፡ በሕያዋን ዘንድ ሲመሰገን ይኖራል።

የሰው ትውልድ፡ አንዱ አልፎ፡ ሌላው እየተተካ፡ የቀደመው ሲረሳ፣ እርሱ እግዚአብሔር ግን፡ ለዘለዓለም የሚኖር ሕያው በመኾኑ፣ ምስጋናውም፡ እንዲሁ፡ ጊዜ የሚወስነው፥ ወይም፡ የሚሽረው ሳይኾን፡ እንደባሕርዩ፡ ለዘለዓለም የሚኖር ነው። ስለዚህ፡ ‘ምስጋና፡ የእግዚአብሔር፡ የባሕርይ ገንዘቡ ነው!’ ይባላል።

ስለዚኽ፡ ‘እግዚአብሔር ይመስገን! እግዚአብሔር ይስጥልኝ!’ የሚለው የምላሽ ቃል፣ ለኹሉ፡ እንደየሥራው፡ ዋጋውንና ውለታውን ለሚከፍል ለባለቤቱ፡ እውነተኛ ምስጋናን የሚያስተላልፍ፡ ጥልቅ መልእክት ያለው፡ የተቀደሰ ባህል ነው። ስለዚኽ፡ ስለተደረገልን አንድ በጎ ተግባር፡ ተገቢና ትክክለኛ የኾነው አጸፋዊ ምላሽ፡ ከላይ እንደተብራራው፡ ‘አመሰግናለሁ’ ሳይኾን ‘እግዚአብሔር ይስጥልኝ’ ይኾናል።

ወደ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ለመመለስ ይኽን ይጫኑት