ራፋቶኤል ሙሉ ወርቁ፡ ላቀረቡት ትችት፡ የተሰጠ መልስ።

አቶ ራፋቶኤል ሙሉ ወርቁ፡ ያቀረቡት ትችት፦

የ፲፰ (18)ኛ ዓመት የልደት በዓሌን ሳከብር አባቴ የሰጠኝ ስጦታ አንድ መጽሓፍ ነበር ታዲያ ከታላቅ መልእክት እና ፍቅር ስለሰጠኝ የመጽሓፉ ደራሲን እና መጽሀፉን በጣም እወደቻው እና አከብራቸዋለሁ ፡ ኢትዮጵያ በማንነቱ ፍለጋ ሲሆን መጽሓፉ ደራሲው ንቡረ እድ ኤርምያስ ናቸው። አሁን ግን እኚህ ታላቅ ጸሓፊ Ethiopia the kingdom of God/ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት በተሰኘው ድህረገጻቸው (የኅዋ ሰሌዳቸው) ይዘት ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ማኅበረ ኤልያስ (ሥላሴ?) ዘደቂቀ ኤልያስ ከተሰኘው ማኅበር ይዘት ጋር የሚመሳሰል መልእቶችን የሚያንጸባርቁ ሲሆን ምእመናን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ላይ ያላቸውን ፍቅር እና እምነት የሚያላሉ እና ቤተክርስትያናን ለሁለት የሚከፍል አስተምህሮት በጽሁፎቻቸው ሲያቀርቡ ማስተዋሌ ከርሳቸው ይልቅ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ያለኝ ፍቅር ይልቃልና በጥርጣሬ እንደመለከታቸው እያደረገኝ ነው።

በማስከተልም፦

አንዱ፡ Ethiopia the kingdom of God/ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግስት የተሰኘው የፌስቡክ ድህረ ገጽን (የኅዋ መድረክን) አቋም እንደሚከተለው አንጸባረቀልኝ፦

ደግሞም፡ እግዚአብሔር ጥንቱኑም፡ የመሠረተውና በቃል ኪዳኑ ያጸናው፡ ሥርዓተ ጋብቻን ማዕከል አድርጎ፡ የሚመራውንና የሚካኼደውን፡ ቤተ-ሰብአዊ የአኗኗር ሥርዓትና ሕይወት እንጂ፥ በዱርና በገደል የሚደረገውንና የሚካኼደውን፡ የአኗኗር ሥርዓትና ሕይወት፡ ያለመኾኑን፡ በኢየሱስ ክርስቶስነቱ በተገለጸበት ጊዜ፡ ገሃድና ይፋ አውጥቶታል። 

እንግዲህ እነዚህ ሰዎች በዱር እና በገደል የሚሉት የአባቶቻችንን የምኩስና ሕይወት ነው በርካታ አባቶች ይህችን ሀገር በጸሎት እየጠበቁ የሚገኙት በየበረሃው ባሉ ገዳማት ውስጥ ነው ታዲያ እነዚህን አባቶች ጠላት አድርጎ የኦርቶዶክ ተዋህዶ ተቆርቀሪ ነኝ ማለት የበግ ለምድ ለብሶ የቅዱሳንን ስም እየጠሩ ኦርቶዶክስን ለመጣል የተዘረጋ ወጥመድ እንደሆነ ነው የሚያመለከተኝ!!! ወገን ማሰተዋል ይበጃል . . . .እኔ እኮ የሚገርመኝ ማህበረ ቅዱሳን እና የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አካላት ለምን እንደዚህ አይነት አካላትን በዝምታ እንደሚመለከታቸው ነው!!!''

ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ ለአቶ ራፋቶኤል ሙሉ ወርቁ ሒስ የተሰጠ መልስ፦

አቶ ራፋቶኤል! ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥትን፡ እስካኹን አላወቋትምን? አያምኑባትምን? ልጇና ነጋሢዋ፥ ካህኗና ዜጋዋ መኾንን መምረጥ አልፈለጉምን? የራሷ ፃማ ሀብቷ የኾነው፡ "ተዋሕዶነት" እንጂ፡ የኋለኛነትና የተከታይነት፥ የቅኝ ተገዢነትና የኑፋቄ መታወቂያና ማረጋገጫ ምልክት የኾነው "ኦርቶዶክስነት"፡ ለእርሷ፡ ምኗም እንዳልኾነ፡ እስከዛሬ አልተገነዘቡምን?

በቅድሚያ፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች፡ መልስ ሊሰጡ ይገባል። መልስዎ፡ በሙሉ፡ አዎንታዊ በኾነ ኖሮ፡ ገንቢ ውይይታችንን በቀጠልን ነበር፤ ነገር ግን፡ እንዲህ ስላልኾነ፡ እርስዎንና እኛን የሚያገናኘንና የሚያነጋግረን፡ አንዳችም ምክንያት ስለሌለ፡ የአሳብ ልውውጣችንን፡ እዚሁ ላይ ማቆም ግድ ይኾንብናል። ይኹን እንጂ፡ የበጎ አስተዋዮችና የቅን አንባቢዎቻችን፡ የእውቀት አድማስ ይሰፋ ዘንድ፡ እርስዎ በሠነዘሯቸው የሒስ አስተያየቶችዎ ውስጥ፡ ላወሷቸው የትችት ነጥቦች፡ የምናብራራው ቍም ነገር ስላገኘንበት፡ ያንን፡ ከዚህ እንደሚከተለው ባጭር አቅርበናል።