ቀን የሚቀየረው በስንተኛው ሰዓት ነው?
፩. ዕለት (ቀን) የሚቀየረው፡ ከእኩለ ሌሊት፥ ማለትም፡ ከጨለማው ፮ኛ (ስድስተኛ)፥ ወይም፡ ከዕለቲቷ ፳፬ኛ (ሃያ አራተኛ) ሰዓት በኋላ ባለችው ቅጽበት ነው፤ ምክንያቱም፡ መሬት፡ በፀሓይ ዙርያ የምታደርገው፡ የ፩ (አንድ) ዕለት፥ ማለትም፡ የ፳፬ (ሃያ አራት) ሰዓታት፥ ወይም፡ የ፷ (ስድሳ) ኬክሮስ ዑደት አብቅቶ፡ የአዲሱ ዕለት ዑደት፡ ፩ ኬክሮስ፥ ወይም፡ ፩ ሰዓት ተብሎ የሚጀመርበት፡ የጊዜ ቀመር (አቈጣጠር) መነሻ፡ በዚያች በእኩለ ሌሊቷ አፍታ ላይ ስለኾነ ነው።
እኩለ ሌሊት፥ ማለትም፡ የጨለማው ጊዜ ፮ኛ፥ ወይም፡ የዕለቱ፡ ፳፬ኛ ሰዓት፡ ከዑደቱ ኺደት ዓናት፥ ወይም ቍንጮ፥ ወይም፡ ጫፍ ከደረሰ በኋላ፡ "ውድቅት" የተባለውን፡ የማዘቅዘቅ ርደቱን ወጥኖ፡ የንጋት ፍንጭ የኾነው የጎህ መቅደድና የፀሓይ ብርሃን ውጋጋን፡ የመፈንጠቁ ነፀብራቅ፡ በስተምሥራቁ አድማስ በኩል መታየቱ የሚጀመርበት አፍታ ነው።
በእኩለ ሌሊት አንጻር፡ እኩለ መዓልት (ቀን)፥ ወይም፡ "ቀትር" የሚለው ጊዜ፥ የዕለቱ እኩሌታ የኾነው፡ የ፲፪ኛውም ሰዓተ ጊዜ ማዕከል ይገኛል። እንደእኩለ ሌሊቱ ኹሉ፡ ይህም፡ 'እኩለ መዓልት"፥ ወይም "እኩለ ቀን"፡ የመዓልቱ (የብርሃኑ) ጊዜ ፮ኛ ሰዓት፡ "ቀትር" ከተባለው፡ ከዑደቱ ኺደት ዓናት፥ ወይም ቍንጮ፥ ወይም፡ ጫፍ ከደረሰ በኋላ፡ የማዘቅዘቅ ርደቱን፡ በሠርኩ ጎዳና ላይ በመወጠን፡ የፀሓይዋ ብርሃን እየቀነሰና ሙቀቷም እየቀዘቀዘ ኼዶ፡ ይህችው ጀንበር እያቈለቈለች፡ የምሽት ጥላዋን፡ በስተምዕራቡ አድማስ በኩል፡ ዘርግታ በማልበስ፡ጊዜዋን፡ ለጨለማው ለማስረከብ፡ የመጥለቋ ኺደት መጀመሩ የሚከሠትበት አፍታ ነው።
፪. መሬት፡ በ፳፬ ሰዓቶች ውስጥ፡ ፀሓይን ፩ ጊዜ እንድትዞር በማድረግ፡ ፈጣሪ፡ ፩ ዕለትን የሚያስገኝ ሥርዓትን እንደሠራ ኹሉ፡ እንዲሁ፡ መላዎቹ ፍጡራኑ ኹሉ፡ ይህንኑ አንዱን ዕለት፡ ተወዛውዘውና ተንቀሳቅሰው እንዲኖሩበትና እንዲሠሩበት፥ እንዲያርፉበትና እንዲተኙበትም፡ ለእነዚሁ ፍጡራኑ አመቻችቶ አደላደለላቸው።
ይኸውም፡ ፳፬ ሰዓቶች ያሉትን፡ አንዱን ዕለት፡ ለኹለት እኩል ከፍሎ፡ ፲፪ (አሥራ ኹለት) ሰዓታት ባሉት፡ "መዓልት"፥ ወይም፡ "ቀን" በተባለው፡ በአንዱ እኩሌታ፡ ፀሓይ፡ በብርሃኗና በሙቀቷ ሠልጥናበት፡ ጸጋዋንና አገልግሎቷን፡ ለፍጥረት እንድታበረክትበት፥ በሌላው በቀረው፡ ፲፪ (አሥራ ኹለት) ሰዓታት ባሉት፡ "ሌሊት"፥ ወይም፡ "ጨለማ" በተባለው፡ በአንዱ እኩሌታ ደግሞ፡ ጨረቃ፡ በነፀብራቋና በለብታዋ ሠልጥናበት፡ ጸጋዋንና አገልግሎቷን፡ ለፍጥረት እንድታበረክትበት በመደንገጉ ነው።
በዚህ መሠረት፦
አ. ፳፬ ሰዓታት ያለው፡ የዕለቱ፡ የጊዜ አቈጣጠር መነሻው፡ ከሌሊቱ ፮ ሰዓት ኾኖ፡ መድረሻው ደግሞ፡ ዞሮ፡ እስከሌሊቱ ፮ ሰዓት የኾነው፣
በ. ለእያንዳንዳቸው፡ ፲፪፥ ፲፪ ሰዓታት ያላቸው፡ የመዓልቱና የሌሊቱ፡ የጊዜ አቈጣጠር መነሻና መድረሻ፡ የመዓልቱ፡ መነሻው፡ ከንጋቱ ፲፪ ሰዓት ኾኖ፡ መድረሻው፡ እስከምሽቱ ፲፪ ሰዓት፣ የሌሊቱም፡ መነሻው፡ ከምሽቱ ፲፪ ሰዓት ኾኖ፡ መድረሻው፡ እስከንጋቱ ፲፪ ሰዓት የኾነው፡ ለምን እንደኾነ፡ ምክንያቱን፡ ከላይ ባጭር የተሰጠው ሓተታ ያስገነዝባል።
ከዚህ የተነሣ፡ በአንድ በኩል፡ ሙሉ ፳፬ ሰዓቶች የተሰጡት፡ የአንዱ የዕለት ጊዜ ቅመራ፥ በሌላው በኩል ደግሞ፡ ለእያንዳንዳቸው፡ ፲፪፥ ፲፪ ሰዓታት ተወስኖ የተሰጣቸውን፡ "መዓልት" የተባለውን፡ የብርሃኑን ጊዜና "ሌሊት" የተባለውን፡ የጨለማውን ጊዜ ያካተተውን ቅመራ፥ እነዚህን፡ ኹለት ዓይነት ባሕርያትና አገልግሎት ያላቸውን ሥርዓቶች፡ በአንድ ዓይነት፥ ወይም፡ በተመሳሳይ የጊዜ ቀመር ለማዋሓድ እንደማይቻል ግልጽ ነው።
ይህ እውነታ፡ ለ፯ሺ፭፻፰ ዓመታት ጸንቶ በቆየው፥ በብሉያቱ ኾነ በሓዲሳቱ የቅዱሳት መጻሕፍት ኪዳናት ውስጥ ተመዝግቦ በሚገኘውም፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ሥርዓት ዘንድ፡ እስካኹንና ለወደፊትም የሚሠራበት መኾኑ ይታወቃል።