በቅዱሱ ኪዳን ሕፃናት የተፈጸሙ፡ ታላላቅ ተኣምራት።

ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ ለቅዱሱ ኪዳን
ኢትዮጵያውያትና ኢትዮጵያውያን!
በጠቅላላም፡ ለክቡራንና ክቡራት አንባቢዎቻችን!
_______________

     ሕያውና መለኮታዊ ስለኾነው፡ የግእዝ ቋንቋችንና የፊደል ገበታችን፡ እግዚአብሔር፡ በኢትዮጵያውያኑና በኢትዮጵያውያቱ ሕፃናት፥ በሞግዚት ወላጆቻቸውም መሣሪያነት፡ የፈጸመውን፡ ዕፁብና ድንቅ ተኣምራት፡ በመንፈሳዊ አትኵሮትና ተመሥጦ ኾናችሁ ትከታተሉት ዘንድ፥ ደግሞ፡ እናንተም፡ እያንዳንዳችሁ፡ ራሳችሁን፡ ለዚህ፡ የተቀደሰ በረከት፡ ታበቁ ዘንድ፡ ይኸው፡ የተኣምራቱን፡ የምሥራችና የትፍሥሕት ዜና፡ እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበንላችኋል።
     በዚህ መልእክት፡ “ሞግዚት’’ የሚለው ቃል፡ ግእዙ፡ ወንዱን፡ “መግዝእ’’፥ ሴቷን ደግሞ፡ “መግዝእት’’ ብሎ፡ በኹለት ጾታ የሚለያቸውን፡ ሐፀንት (ሕፃናት አሳዳጊዎች)ን የሚያጠቃልልና የሚወክል ይኾናል።