እንኳን፡ ለ፪ሺ፲፩ (፳፻፲፩)ኛው ዓመተ ምሕረት፡ በዓለ ትንሣኤ: በያለንበት አደረሰን!
ይደረስ፦ በምድርና በሰማያት በመላችው፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ዕቅፍ ውስጥ፡ የእግዚአብሔርና የኢትዮጵያ ልጆች፣ ነጋሢዎችና ካህናት ኾናችሁ፡ "ኢትዮጵያ" በተባለችው የዐፅመ ርስት አገራችሁ ሠፍራችሁ፥ በኪዳናዊው ኢትዮጵያዊ የጨውነት ህልውናችሁና የመብራትነት ተልእኳችሁም፡ አልጫና ጨለማ በኾነው፡ በዓለሙ ኹሉ አህጉራት፡ በመለኮታዊው ዕቅድ ተዘርታችሁና ተሠራጭታችሁ፣ ተልካችሁና ተመድባችሁ፡ በቀዳማዊቷ የትንሣኤና በዘለዓለማዊቷ የሰንበት ሕይወት ለምትኖሩ፡ የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ወገኖቻችን ለኾናችሁት፡ ኪዳናውያን ወንድሞችና ኪዳናውያት እኅቶች ኹሉ! በያላችሁበት!
በእግዚአብሔር አብወእም ድንግል ማርያም፥ በእግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ መሲሕ እና በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስም ኢትዮጵያዊዉን ሰላምታችንን፡ እናቀርብላችኋለን።
ከ“በዓለ-ኢትዮጵያ” ጋር ተያይዞ የመጣውን “ዓቢይ ጾምን” (ሁዳዴን)፡ በዚያው መንፈስና ሥርዓት ቀጥለን፥ በዓለ ሆሣዕናንና ሕማማትንም፡ በመልካም ፈጽመን፡ በእግዚአብሔር ቸርነት፡ ከበዓለ ትንሣኤ ልንደርስ ችለናል። ስለዚህ፡ እጅግ ደስ ሊለን ይገባል።
እንዲህ፡ ኢትዮጵያዊና ኪዳናዊ ደስታችንን ከመግለጽ ጋር፡ ለእያንዳንዳችን ሕይወት፥ለአገራችን ማንነትና ለመላው ዓለም የምንነት መታደስና ትንሣኤ፡ እውን ማረጋገጫ ስለኾነው፡ ስለሰላማችን ኢየሱስ መሲሕ ትንሣኤ፥ እስከበዓለ መንፈስ ቅዱስ ድረስ ስላሉትም በዓላት፡ የተዘጋጀውን፡ የመልእክታችንን ሓተታ አቅርበንላችኋልና፡ ተመልከቱት!