ከመርዓዊ ጐሹ የደረስን ቅኔያዊ መልእክትና ለዚያ የተሰጠ ምላሽ።

ከመርዓዊ ጐሹ የተላከ።

ንቡረ፡እድ፡ኤርሚያስ፡ የሚከተለውን፡ቅኔ፡በጉባኤ፡ላይ፡አቅርቤው፡ነበር፡፡ያሎትን፡አስተያየት፡ቢሰጡኝ

መወድስ
ስመ፡አብ፡ወወልድ፡ወመንፈስ፡ቅዱስ
ፈጠሩ፡ሔዋን፡ወአዳም፡ይፈጥሩ
ዘዘነጽራዎ፡ዓይነ፡ይሄጽሩ
ዘዘኦዱ፡ዘዘኦዱ፡ዘዘኦዱ፡ዘዘየአውዱ፡ዘዘኦዱ፡ሠምሩ
አብርሃም፡ወይስሐቅ፡ሙሴ፡ወአሮን፡ፍና፡ኃቅለ፡ሲና፡ይትባደሩ
አበው፡እስራኤል፡ይትናገሩ
ሄሱ፡አርዮስ፡ወንብረ፡እድ፡(ኤርሚያስ)፡ይጻረሩ
ሊቀ፡ነቢያት፡ኤልያስ፡እብነ፡ሥላሴ፡ይዌሩ
ለዕለተ፡ሰንበት፡ፀላኢሃ፡አርዌ፡ገዳማት፡ከመ፡ይገሩ
ሊቀ፡ነቢያት፡ኤልያስ፡እብነ፡ሥላሴ፡ይዌሩ፡፡

ከንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ የተሰጠ ምላሽ።

ይድረስ፡ ለአቶ መርዓዊ ጐሹ!
     ለላኩልኝ መወድስ ቅኔ፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ!
     "በጉባኤ ላይ አቅርቤው ነበር!" ላሉት፡ ለዚሁ ቅኔዎ፡ እንድሰጥዎ የጠየቁኝ አስተያየት፡ ከዚህ የሚከተለው ነው፦ 
        ቅኔ፡ በመሠረቱ፡ በአንድ ግለሰብ መንፈስ የሚደረስ፡ የግጥም መድበል ስለኾነ፡ ምሥጢሩንና መልእክቱን፡ በትክክል ገልጦ ማስረዳትና ማብራራት ያለበት፥ ይህን ማድረግ የሚቻለውም፡ ያው ራሱ፡ ገጣሚው ብቻ መኾኑ እሙን ነው።
        በዚህ ዓይነት፡ ይህን የእርስዎን ቅኔ፡ እኔም ኾንሁ፡ ሌላው ሰሚው፥ ወይም፡ አንባቢው፡ በእየራሱና ለእየራሱ፡ በፈለገው መልክና ይዘት ሊተረጉመው ስለሚችል፡ በዚህ በእርስዎ ቅኔም፡ ይህ ዐጉል ዕድል ሊደርስበት አያስፈልግም።
         ስለዚህ፡ ይህንኑ ቅኔዎን፡ ከዚህ ዐጉል ዕድል ለማዳን፡ በቅድሚያ፡ ራስዎ፡ ወደኢትዮጵያኛ (ዐምሓርኛ) ተርጉመውና ምሥጢሩን ገልጠው፥ የሰምና ወርቅ ሓተታውንም ተንትነውና አብራርተው፡ ለእኔም ኾነ፥ በተለይ፡ ለሌሎቹ አንባቢዎቻችን  እንዲያቀርቡት፡ ወደእርስዎ መልሼልዎታለሁ።
        አለዚያ፡ እንዲያ ካልኾነ፡ እኔ፡ ለዚህ ቅኔዎ ተገቢ የኾነውን መልስ፡ በሌላ መወድስ ቅኔ ልስጥ ብዬ ብሞክር፡ እኔም፡ እንደእርስዎ መኾኔ ነው። ምክንያቱም፡ እኛ፡ የእግዚአብሔርና የኢትዮጵያ ልጆች፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የምንኖረው፡ የሙታንን ኑሮ ሳይኾን፡ የሕያዋንን ሕይወት ስለኾነ፡ የምንነጋገረውና የምንጻጻፈው፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ሥርዓት ተከትለን፡ በእርሱ እውነትና ብርሃን፡ በግልጥና በገሃድ በመነጋገርና በመጻጻፍ እንጂ፡ ሌላው እንደሚያደርገው፡ በባዕዱ ሓሰትና ጨለማ፡ በምሥጢርና በአሽሙር ንግግርና ጽሕፈት አይደለም።
        እግዚአብሔርም፡ ጥንቱኑ፡ ፍጥረቱን ሲያስገኝ፥ ለመጀመሪያዎቹም ፍጡራኑ ያሳወቃቸውን የሕይወት መመሪያ ሲያሰማቸው፥ በየጊዜውም፡ ለፍጥረቱ የሚያስተላልፈውን መልእክት የሚያደርሰው፥ በመጨረሻውም ዘመን፡ ወደዚህ ዓለም፡ በሰውነት አካል መጥቶ፡ በመስቀል ላይ ዕርቃኑን በመዘርጋት፥ ቀጥሎም፡ በበዓለ ሃምሳ፡ በመንፈስ ቅዱስነቱ፡ በሰዎች ላይ በምልዓት ወርዶ፡ የዓለም ቋንቋዎችን አንድ በሚያደርገውና ኹሉም በሚገባቸው፡ በአንዱ የግእዝ ልሳን፡ መልእክቱን፡ ለኹሉ በማዳረስ፡ ምንነቱንና ማንነቱን የከሠተው፥ በጠቅላላ፡ የፈጣሪነት ሥራውን ኹሉ ያካኼደውና ያከናወነው፥ እያካኼደና እያከናወነም ያለው፡ በፍጹም ግልጥነትና ገሃድነት ብቻ እንደኾነ የታወቀ ነው
        በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ዘንድ፡ በዚህ ረገድ ኾነ በሌላው ኹሉ፡ ዛሬና ወደፊት፥ ምንጊዜም፡ ሕያው ኾኖ በተግባር ላይ ውሎ የሚሠራው፡ ይኸው እግዚአብሔራዊው ሥርዓት እንጂ፡ ሰውኛው እንዳልኾነ፡ እርስዎም፥ እርስዎን የመሰሉትም ኹሉ፡ እንድታውቁት ይኹን!