ከአባ ወልደ-አረጋዊ (አባ ዳንኤል ተጫኔ)፡ ለሦስተኛ ጊዜ፡ የተላከ መልእክት።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ!
ለንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ ለተሰጠው መልስ እኔ አባ ዳንኤል ተጫነ አግዜ የምሰጣቸው መልስ ይህ ነው፡፡
“ ታጠፏቸው ዘንድ አይቻላችሁም፡፡ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ “ የሐዋርያት ስራ ፭፡፫
ይህ አማናዊ ቃል ተፈፀመቦት፡፡
“በቅድሚያ ግን በዚህ ስምና ብርሃናዊ የስዕል መልክ በትክክለኛ ማንነታቸው አባ ወልደ አረጋዊ ወልደ ሥላሴ የተባሉት ሰው.” በማለት የአንባቢን ልቦና ለማደናገር የሰነዘሩት ሀሰት እራሶን የመዘነ ሆነ፡፡ ለመሆኑ እንደ እርሶ ካለ የእድሜ ባለጸጋ ሰውን በሀሰት ለመወንጀል መሞከር ይጠበቃል? አባ ዳንኤል ተጫነ ትክክለኛ ማንነቴ መሆኑን ይወቁ፡፡ እናትና አባቴ ያወጡልኝ የሰጡኝ እስከ አሁን ስጠራበት የምገኝበት፤ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ፤ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተቋማት እና እስከ የሀገሪቱ ሚኒስቴር ቤተ መዛግብት ድረስ ማንነቴን ገልጦ የያዘ መጠሪያ ስሜ ነው፡፡ ሰውን ለማወናበድ አይሞክሩ ፡፡ አያራምዶትምና፡፡ ከእርስዎም ሀሰት መናገር አይጠበቅምና፡፡ እራሶን ያቀሎታል፡፡ ይመዝኖታል፡፡ የእኔን የኋላ ማንነት የሚያውቁ ሁሉ በፌስ ቡክ መድረኮ ላይ ያሰፈሩትን ስም ማጥፋት እያስተዋሉት ነውና ትዝብት ላይ ጣሎት፡፡ በሀሰት በተጀመረ መልእክት እውነት እንደማይገኝ ደመደሙቦት፡፡ ለወደፊት አይድገሙት፡፡
እኔን ለመታዘብ አንባቢም እንዲታዘብ አስበው “ለትዝብት እና ለአይነት ያህል ጠቅሻቸዋለሁ፡፡ ከበርካታዎቹ መካከል አንዱ የእርሳቸው ፅሁፍ 'የእውነት ልጅ ኑብረ እድ ኤርሚያስ ከልብ እንወዶታለን፡፡ እባኮ ለዚህ ክፉ ትውልድ ቁርጥ ፍርዶን ያስተላልፉ! ሁሉ ይወቀው! የኢትዮጵያ ስውራን ስለ እርሶ አብዝተው ሲጮሁ አየሁ፡፡ ምንኛ የታደሉ አባት ኖት፡፡ እርሱ ይፍቀድና አይኖትን ያሳየኝ፡፡ አባቴ እንቁ ኖት! ግን ያወቀዎት የለምእና እናዝናለን፡፡ ' ታዲያ የአሁኑ ፅሁፎ እውነተኛ ማንነቶን እና ምንነቶን ተልእኮዎም ምን እንደሆነ ያጋለጠ ከመሆኑ ጋር እራሶን 'በአንድ ራስ ሁለት ምላስ' ያሰኘዎ አልሆነምን? አዎን! በርግጥ አሰኘዎ እንጂ” ላሉት አይሳሳቱ፡፡ የማደርገውን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ በማስተዋልም እራመዳለሁና በአንድ ራስ ሁለት ምላስ መቼም አልሆንም፡፡ ይብላኝ ለእርሶ ሰውን በምን ላጥቃው ብለው ቃላት ለሚቆፍሩት፡፡
አዎን ብያለሁ፡፡ ትላንትም ዛሬም ነገም ቃሌ አንድ ነው፡፡ ለዚህም እኔ በስጋ የማውቃቸው ዛሬ የእርሶን የፌስ ቡክ መድረክ የሚከታተሉ ይታዘቦታል፡፡ መፅሐፍቶቾን እንዲገዙ ያደረኳቸው የፊስ ቡክ መድረኮን እንዲከታተሉ ያደረኳቸው ብዙዎች አሉና በሄድኩበት ሁሉ አንደበቴ በክፉ አንስቶዎት አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ያስተምሩዋችኋል፡፡ ስሟቸው፡፡ አድምጧቸው ከማለት ውጪ፡፡
ሀ. ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መቅደሱ እና ዙፋኑ ነች፡፡ ይህንን ታላቅ ምስጢር በመፅሐፍቶቾ ፅፈው በመመስከሮ፡፡
ለ. ኢትዮጵያ የዓለሙ መፋረጃ መሆኗን ስለመሰከሩ ፡፡
ሐ. እውነተኛው ማህተማችን ( የአንገታችን ማህተብ ) ቀስተ ደመና ነው ብለው ስለ መሰከሩ፡፡
መ. አንዲቷ የቀደመችው ጠባቧ መንገድ ተዋሕዶ ናት፡፡ የእኛነታችን መገለጫ ርትእት ሐይማኖታችን ብለው ስለመሰከሩ፡፡ ኦርቶዶክስ የሚለውን የኑፋቄ ስም ስለተቃወሙ፡፡
ሠ. ጥልቅ ሐይማኖታዊ ምስጢር ያነገበውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ በመሀሉ አንበሳው መስቀል ይዞ የሚታይበትን የሐገራችን ባንዲራ ትርጉም እና ሚስጢር ገልጠው ስለመሰከሩ፡፡
ረ. እነዚህንና ሌሎች እንደ ወርቅ የጠሩ ሚስጢራትን ስለፃፉ፤ በዚህም ምክንያት በዘመነ ደርግ ሰማእትነትን ስለከፈሉ፡፡
አዎ አባቴ እንቁ ኖት ብያለሁ፡፡ ታዲ እውነትን መካድ ነበረብኝ? መቼም አላደርገውም፡፡ እውነት ሲናገሩ ነገም እቀበሎታለሁ፡፡ ሲሳሳቱ ደግሞ ተሳስተዋል እል ዘንድ እውነት ታዘኛለች፡፡ እርሶ ግን ይብላኝሎት የተናገሩትን እያጠፉት ነውና፡፡
“በእርሶ እና እርሶን በመሳሰሉት የፀረ ኢትዮጵያ ሐይላት ጎራ በኩል እተነዛ ያለውን ሀሳዊ መልእክት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ደረስኩበት፡፡ ያም እናንተ ለቴዎድሮስነት ያጫጭሁት እና ያዘጋጃችሁት እርሱም ለዚህ እራሱን ያጨ እና ለዚሁ ያዘጋጀ አንድ ሰው መኖሩን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡” ላሉት
ሎቱ ስብሀት! የኢትዮጵያ አምላክ አጋእዝት ሥላሴ ይቅር ይበሎት፡፡ ህዝብን ማወናበድ እና ግራ ማጋባት ምን ይጠቅሞታል? የትስ ያደርሶታል? ትግል ከመለኮት እስከ የት? ያልኮት ለዚህ ነው፡፡ የፈለገ የሀሰት እና የማወናበጃ ወሬ እና መልእክት ብታናፍሱ እውነትን ለመሰወር አትችሉም፡፡ ለዚህ ነው ታላቁ ሊቅ የአይሁድ መምህር የነበረው ገማልያል ለእርሶ እና ለመሰሎችዎ እውነትን ለማድበስበስ ለሚነሱ ሁሉ “ ታጠፏቸው ዘንድ አይቻላችሁም” ብሎ የገሰፃችሁ፡፡
እኛ መንግስተ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ ለቴዎድሮስነት የምናጨውና የምናዘጋጀው እርሱም እራሱን ያጨ እና እራሱን ለዚህ ያዘጋጀ ሰው እንደ ሌለንና ሊኖረንም እንደማይችል እንደማይገባም የለቀቅናቸው አዋጆች ገልጸዋል፡፡ ዳዊት በመዝሙሩ “በዚህ ዘመን የሰው ልጅ እድሜ ቢበዛ ሰባ ፣ ሰማኒያ ነው” እንዳለ እና እንደተናገረ አልፎም እስከ መቶ አመት እድሜ ያለው አንድን ሰው ለቴዎድሮስነት የምናጭ አይደለንም እርሶ እና መሰሎቾ እንደሚያናፍሱት ተራ አሉባልታና ሐሜት ፡፡ አበው ቅዱሳን ንፁሐን ኢትዮጵያውያን በእንቁ የብራና መፅሐፍቶቻቸው አስረግጠው ፅፈውልናልና ፡፡ ይብላን ለእርሶ!
የእኛን ቴዎድሮስ ይወቁት፡፡
እርሶ በካዱዋቸው ቅዱሳን ለ፪ሺ ዘመን በእንባ እና በለቅሶ በፆም እና በስግደት እተማፀኑ በተስፋ ሲጠበቅ የቆየው ቴዎድሮስ!
ጌታም በቅዱስ ወንጌል ለጸሐፍት ፈሪሳውያን ይህንን መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አንፀዋለሁ ብሎ ከራሱ ትንሳኤ ባሻገር ስለ መጨረሻው ዘመን አመስጥሮ የተስፋ ቀነ ቀጠሮ የተሰጠለት ቴዎድሮስ!
ከሦስት ቀን በኋላ በከሀዲያን የፈረሰውን የተዋሕዶ መቅደስ የሚያንፀውን ቴዎድሮሳችን ምድር እና ሰማያት የሚንቀጠቀትለት፣ መልአክት የሚያገለግሉት፣ ቅዱሳን እየቦረቁ የሚከተሉት እኛም ስንጠብቀው የቆየውንና ሰዓቱ ዘመኑ ደርሶ የነገሰልንን፤ ከዚህም በኋላ በስጋዊ የንግስና ዙፋን ተቀምጦ ይነግሳል ብለን ማናስበውን ቴዎድሮስ ይወቁት!! በሐሜት አይጎዱ፡፡ ሀሰትም አያውሩ፡፡
ሁሉን ሊፀዳ የሚመጣው እርሱ መሆኑን ለረዳት እስቲ ይህን የነቢያት ቃል እናስተውል፡፡ “ ነገሥታቱን በሞት ወደ መቃብር አወረዳቸው፡፡ የከበሩ ነገስታትንም ከዙፋናቸው እየገለበጠ ጣላቸው፡፡ በኮሬብ እና በደብረ ሲና የተሰራውን ሕግ ቢያፈርሱ መቻያ የሚያመጣ እርሱ ነው፡፡ . ሲራክ 48፡ 6-7
በአሁኑ ሰዓት ለኛ ነግሶልን ያለው ቴዎድሮስ ይሄ ነው፡፡ በአህዛብ ደባ እና ተንኮል ፈርሳ የነበረችውን የተዋሕዶ መቅደስ መልሶ ያነፀ፣ ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ወልድ ዋህድ ኢትዮጵያ ሀገረ ማርያም እመፍጥረት፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ዋህድ የተዋህዶ አንበሳ ማርያም እመፍጥረት የተዋሕዶ ጣዕዋ፡፡ ኢትዮጵያ ተነስታለች አንበሳው አግስቷል፡፡ ኢትዮጵያ በተዋህዶ ዓለምን አንድ አድርጋ እየገዛች ነው፡፡ ብሎ እያወጀ ያለው ቴዎድሮስ ለእኛም አባታችን በእሳት አጽርእቅት ተጠቅልሎ መላእክት ያዋለዱት፣ ስለ አምላኩ ሕግ ቀናኢ ሆኖ አራት መቶ ሐምሳ የበዓል ካህናትን ያጠፋ ፣ ንጉስ አካዚያስ ወደ እርሱ የሰደዳቸውን ሁለት ሐምሳ አለቆች እና መቶ ሰዎች እሳት ከሰማይ አውርዶ ያጠፋ፣ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይን የለጎመ፣ በእሳት ሰረገላ በእሳት ፈረሶች ተጭኖ በአውሎ እና በድብልቅልቅ ረድኡ ኤልሳን ተሰናብቶ ወደ ብሔረ ሕያዋን ያረገው ቅዱስ ኤልያስ እውነተኛ የእግዚአብሔር አምልኮ በዓለም ሲጠፋ እውነተኛይቱ የተዋሕዶ መቅደስ ስትፈርስ፣ ዓለም በሀሳዊው ወጥመድ ሲወድቅ ሁሉ ከክብር ሲጎድል በተሰተው ቀነ ቀጠሮ በሦስተኛው ቀን ማለትም ከጌታ እርገት በኋላ ፪ሺ ዘመን ተፈፅሞ ፫ተኛው ሺ ሲገባ በሀገራችን አቆጣጠር በ፪ሺ ዓ.ም በታላቅ ኃይልና ስልጣን ቅዱሳንን ሁሉ አስከትሎ ከብሔረ ሕያዋን የመጣው ቅዱስ ኤልያስ የእኛ ቴዎድሮስ እርሱ መሆኑን ይረዱ፡፡ አይሳቱ፡፡
ይህን ምስኪን የሚሄድበት አጥቶ በዕንባ ፈጣሪውን እየተማፀነ የሚገኘውን ሕዝብ አታወናብዱት፡፡ ሕይወቱን አታጨልሙበት፡፡ ስለእውነት ቁሙ! የኢትዮጵያ ጠላቶች በሆኑ በባዕዳን ሀገራት ተደብቃችሁ ግራ አታጋቡት፡፡ ግቡ ወደ አገራችሁ፡፡ ተዋሕዶን ፣ አንዲቷን ዕለተ ሰንበትንና ሕግ እና ነቢያትን አውጁ፡፡ከሚራበው ወገናችሁ ጋር ተራቡ፡፡ ከሚያለቅሰው ወገናችሁ ጋር አልቅሱ፡፡ ይህ ነው ኢትዮጵዊነት፡፡ ባሕር ማዶ መሽጎ ማውራት አይደለም፡፡
እኛ መንግስተ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ ስራችን ግልጥ ነው፡፡ ኃያል ባለስልጣን ቅዱስ ኤልያስ አውሬውን ሊያስረው መገለጡን፣ አንዲቷን ርእትእት ተዋሕዶ ሐይማኖት፣ ሰንበት እረፍትን እና ሕግ እና ነቢያትን ገልጧል፡፡ የተዋሕዶ መቅደስ ታንፃለች፣ ዓለም በፍርድ ላይ ነው፡፡ ግዜው ተፈፅሟል፡፡ኃያል ባለስልጣን ቅዱስ ኤልያስ በጽኑ ስልጣኑ ይህን ዓለም በጎርፍ በነፋስ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ ፣ በጦርነት፣ በበሽታ፣ በኢኮኖሚ ውድቀት እና በሰላም ማሳጣት እየገሰጸው ነው፡፡ ኢትዮጵያን መቅደሱ እና ዙፋኑ አድርጎ ተገልጧል፡፡ በዚህ ነው በዚያ ነው አይባልም፡፡ በፈለገው ሰዓት እና ደቂቃ በፈለገው ቦታ ሁሉ ከቅዱሳኑ ጋር አለ፡፡ አመጣጡ ረቂቅ ነው፡፡ ጨርቅ ለብሶ፣ እንጀራ በልቶ፣ በአንድ ቤት አድሮ የሚመላለስ አይደለም፡፡ በመለኮታዊ ስልጣን በረቂቅ ነው፡፡ ይህን እውነት እያወጅን አይደለም? ታዲያ እንዴት ተራ አሉባልታን ተቀብሎ ማናፈስ ከእርሶ ዘንድ ተሰማ? የመጡብኝ “ኤልያስ አንተን ያወቁ በፍቅርህም ያጌጡ የተደነቁ ናቸው፡፡ እኛም ስለ አንተ ደግነት በሕይወት እንኖራለን፡፡” በተባለለት ደግ አባት ላይ ነውና የእናት ጡት ነካሽ መሆኖን እነግሮታለሁ፡፡ በሕይወት ያሉት ከደግነቱ በተነሳ መሆኑን ያስተውሉ! ኤልያስን ክደው የቅዱሳንን አምላክ እየሱስ ክርስቶስን እና እናቱን ድንግል ማርያምን ማወቅ አይችሉም፡፡ እግዚአብሔር መለኮት ቀብቶ ሒድ እንደ እኔ ሆነህ ዓለምን ተፋረድ፤ አውሬውን እሰር፣ ተዋሕዶን አውጅ፣ የቅድስት ምድር የኢትዮጵያን ክብር ግለጥ፡፡ ለዘመናት የተሰራባትን ደባ እና ተንኮል አራግፍ ብሎ የላከውን ኃያል ነቢይ ተቃውመው ባልቆሙ ነበር፡፡
እኔ ደፋር አይደለሁም፡፡ እረሶ ግን ደፈሩ፡፡ “አይሁዳዊነትን በኢትዮጵያዊነት ላይ ሊጭኑ ደፋ ቀና ያሉ” ብለው በቅዱሳን ላይ ቃል ሰነዘሩ፡፡ አቅሞትን አላውቅ አሉ፡፡ ይህን ግዜ ብእሬ ተመዘዘ፡፡ የአምላኬን ትእዛዝ ማልፈፅም እንዳልመስሎ፡፡ ይሄኔ እደፍራለሁ፡፡
የፈለጋችሁትን በሉ ውጡ ውረዱ እውነትን መሰወር ግን አይቻላችሁም፡፡ ከቅዱስ ኤልያስ ክንድም አታመልጡም፡፡ ካልተመለሳችሁ በአመፃችሁ ከቀጠላችሁ ከቁጣው እሳት ትጎነጫላችሁ፡፡ እንኳን እናንተ ዓለምን ጨምድዶ የነበረው አውሬ በኤልያስ እና በልጆቹ ፊት መቆም አልቻለም እና ልቦና ይስጣችሁ፡፡
የእኛ ቴዎድሮስ የሚበላ የሚጠጣ፣ የሚደክም የሚያንቀላፋ፣ የሚቀመጥ የሚተኛ፣ እዚህ ነው እዚያ ነው የማይባል መሆኑን አውቀው ከአሉባልታ ይውጡ፡፡ ኃያል ባለስልጣን በመላአክት እና በቅዱሳን ታጅቦ ዓለምን እተፋረደ እየገሰፀ ያለው ቅዱስ ኤልያስ ደግነቱ ይብዛልን፡፡
ኃያል ባለስልጣን ቅዱስ ኤልያስም ቴዎድሮስነቱ (ንጉስነቱ) ለዓለም ነው፡፡ ንግስናውም በስጋዊ ዙፋን መቀመጥ እንዳይደለ አሁን በዓለም ነግሶ እንዳለ እንረዳ፡፡ ከፊት ለፊታችን በቅርብ ቅፅበት ደግሞ ኃያል ክንዱን በዓለም ተከስቶ
እናየዋለን፡፡ ዛሬ የተሳለቁ ሁሉ ያፍራሉ፡፡ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፡፡ አመጸኞችንም ያቃጥላል ስርና ቅርንጫፍም አይተውላቸውም ተብሎ የተነገረው ይፈፀማል፡፡
ዛሬ በቅድስት ምድር በኢትዮጵያ ልቦናን የሚከፋፍል በደል እየተፈፀመ እግዚአብሔርን ያሳዘነ ስራ እተሰራ የእኔና የእርሶ ወገኖች በደዌ ነፍስ በደዌ ስጋ ተይዘው ከእውነት መንገድ ወጥተው ሀሳዊ መሲህ ነግሶባቸው በከተማችን በአዲስ አበባ ብቻ በቀን የብዙ ሺ ሕፃናት ደም እየፈሰሰ ግብረ ሰዶም በይፋ ነግሶ የሰይጣን አምልኮ በግልፅ እየተፈፀመ ብዙ ዘግናኝ ስራዎች ሲሰሩ፤ ወንድሞቻችን እህቶቻችን አዛውንት እናቶች ሳይቀሩ የከበረ ሰውነታቸውን አጋልጠው እርቃናቸውን ሲሄዱ ሲታዩ፤ ዝሙት ሐሺሽ ጫት ትንባሆ እና ጭፈራ ነግሶ ሐገራችን ሰዶም እና ገሞራ ሆና ይህንን ሊታደግ እግዚአብሔር ያስነሳውንና የመሰረተውን ቅዱሳን የሚመሩትን መንግስተ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ ማህበርን ለመንቀፍ ባልተነሱ ነበር፡፡
እንደውም ሁሉን ሊያስተካክል ከተገለጠው ኃያል ባለስልጣን ቅዱስ ኤልያስ እና ከቅዱሳኑ ጋር አብረው ስለ እውነት ከቆሙ ጋር አብረው ስለ እውነት በቆሙ ነበር፡፡ ግን መቼ አደለዎት!
መንግስተ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ የማንንም እርዳታ አይፈልግምና የሚመሩት እና የቆሙለት የማያንቀላፉ እረኞች እና ጥልቅ ንስር ዓይኖች ስላሉት በፅናት መለኮታዊ ግዳጁን እየፈፀመ ነው፡፡ ይብላኝ ለእርሶ! ለማንኛውም ቅዱስ ኤልያስ በምህረት ዓይኑ ይመልከቶ፡፡ የኒቆዲሞስን እድል ይስጦ እላለሁ፡፡
ውድ ኢትዮጵውያን የሰው ልጆች ሁሉ በግራ በቀኝ የሚነፍሰውን የአጋንንት ድምጽ ሳትሰሙ ነቅታችሁ የቆማችሁበትን ሰዓት በመዋጀት ሊታደገን የቆመውን የቅዱስ ኤልያስ ድምጽ በመስማት እራሳችንን እናድን፡፡ ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ ተብሎ የተፃፈልንን በሀላፊነት እንመልከት፡፡ ማንም እንዳያስተን ሁሉን በእግዚአብሔር ቃል ልንመረምር ይገባናል፡፡ እደግመዋለሁ በአሉባልታ እና ራሳቸውን ከመለኮት በላይ ባስቀመጡ ግብዞች አንደበት ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል መርምሩ፡፡ ዛሬ በሀገራችን እናውቃለን ባዮች ከመብዛታቸው የተነሳ እውነተኛውን ፈልጎ ማግኘቱ ከባድ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ መመኪያችን፣ መነፅራችን ግን ሁሌም የአምላክ ቃል ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ የአምላክ ቃል የነጠረ እውነት ነውና ብዙችንም ይመዝናልና የሚከፋው ይበዛል፡፡ በአባታቸው በዲያቢሎስ ነውና የሚመሩት አንቱ
የተባሉት ሁሉ ጥቅማቸው የተነካ ሲመስላቸው የስድብ አፍን አብዝተው ይከፍታሉ፡፡ ብዙ ሕዝብን በስሜት በማነሳሳት በተነገረው እውነት ላይ ስደትን ያመጣሉ፡፡ ግን ልብ ብለን ልንረዳው የሚገባን በቁጥር ብዙ ሰዎች የቆሙለት ውሸት ጥቂቶች ከያዙት እውነት በላይ ሊሆን አይችልም፡፡ በአንድ ወቅት በዓለም ያሉ ምሁራን ነን ያሉ ሁሉ መሬት እንደ ጠረጴዛ ዝርግና ጠፍጣፋ ናት ብለው የዘመኑን ሰዎች ሁሉ አሳምነው ነበር፡፡ ብዛታቸው ግን ዓለምን ጠፍጣፋ አልደረጋትም፡፡ ዓለም ዓለም ክብ ናት ብሎ የተነሳውም ጋሊሊዮ አንድ ብቻ በመሆኑ አላሸነፉትም፡፡ ዛሬም ይህንን እውነት አስረግጠው የሚያውቁት በቁጥር ጥቂት ቅዱሳን አባቶች መሆናቸውና አብዛኛው ስቶ መገኘቱ እውነትነቱን ሊያጠፋው እንደማይችል ልንገነዘብ ይገባናል፡፡
ቅዱስ ኤልያስ መጥቶ ምን አስተማረ? በእውነት ከእግዚአብሔር መንገድ የወጣ ነገርን አስተማረ? ከአምላካችን እውነተኛ አምልኮ ገሸሽ እንድንል አጉል ትምህርት አመጣ? በርግጥስ ይህ ቅዱስ ነቢይ ይመጣል ተብሎ አልተጻፈለትም ነበር? እኚህ አባት እንደሚሉት ሀሳዊ መሲህ ቢሆን የአምላክን ቃል ተግብሩ፣ ሕግና ነቢያትን ሰንበትን ፍጹም የሆነችውን አንዲቷን ተዋሕዶ ያዙ ብሎ የአምላክን መንገድ ያስተምር ነበር? አባታችን ያወረዱት የስድብ ናዳ ከቅዱስ መፅሐፍት ይሆን ያገኙት? ይህ ይሆን ትክክለኛው የመንፈስ ቅዱስ አካሄድ?
የቅዱስ ኤልያስ መምጣት አያስፈልገንም የቆምነው በእግዚአብሔር መንገድ ነው ብለን የምናምን ከሆነ ስለምን እንፈራዋለን፡፡ መምጣቱ ጥቅማችን እንጂ ጉዳት አይደለምና፡፡
የሚመጣው እኛ ልናጠራው ያልቻልነውን ሊያጠራ ለሚመጣው የዘለዓለም የአባታችን መንግስት ጠማማውን ሁሉ ሊቆርጥ ሊያፀዳ ነውና፡፡ ይህ ደስታችን ሊሆን ሲገባው እራሳችንን ከእግዚአብሔር ቅዱስ ጋር እያወዳደርን ስለምን በትንሽነታችን እንናደዳለን፡፡ የማይሆንስ የማይገባስ ዝቃጭ ቃል ይመጣናል፡፡ ግን አበክሬ እነግሮታለሁ፡፡ አምላክ ኃያል ስልጣን እና ሰይፍ አሲዞ ከላከው ጠራጊ ቃል ወጥቶ የአምላክን መንገድ እከተላለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ከቶም፡፡ ማንም እርሱን ጠልቶ አምላክን ሊወድ አይቻለውምና፡፡ እንደ ቅዱስ ኤልያስም ለእግዚአብሔር አምልኮ እና ሕግ የሚቀና ፈጽሞ የለምና፡፡ እግዚአብሔርም ሁለት ቃል ሁለት አንደበት የለውምና፡፡
እንደ እልኸኛ ሞኝ ሕፃን ልጅ ማሰቡ አይጠቅምም፡፡ ለአምላክ ቃል እሺ አሜን ማለቱ እራስንም ሕዝብንም ያድናል፡፡ የማምነው የቅዱሳንን አምላክ የቴስቢያዊውን የቀናኢውን የቅዱስ ኤልያስን ፈጣሪ እና አምላክ እግዚአብሔርን ነው የምንል ሁሉ እርሱ አምላካችን ያከበራቸውን ቅዱሳን ሁሉ ልናከብር ግድ ይለናል፡፡ እኔ ግን የሚሰማ ቢኖር ይስማ ብዬ ይህንን ያየሁትን እውነት እመሰክራለሁ፡፡ ጥንትም በገዳማት ሳለሁ በበረሀ ከወደቁ ቅዱሳን አባቶች የሰማሁት ሲተገበር አይቻለሁና ስለ ሀቅ እመሰክራለሁ፡፡ በአሉባልታ ሳይሆን አምላክን ምስክር ባደረገ የእውነት ሚዛን ፡፡ በእርግጥም እነዚህ ከተማ ለአኗኗራቸው ላሉበትም ስነ ምግባር የማይስማማቸው ቅዱሳን ያዩትን ይመሰክሩ ዘንድ ከቅዱስ ኤልያስ ታዘው የሚናገሩትን ሁሉ በማይሻረው ቃሉ መርምሬ ተቀብዬዋለሁ፡፡ ማንም ስለ እዚህ እውነት እናገራለሁ ቢል በቅዱሳን መፅሐፍትና በቅዱሳን ቃል መዝኖ ሰፍሮ ያሳየን እንጂ ተራ አሉባልታ እና ስድብ ትርጉም እንደሌለው ሊረዳ ይገባዋል፡፡ መቼም ይሄንን ለንቡረ እድ የማስተምር ሆኜ አይደለም ፅሁፋቸው ከእርሳቸው የማልጠብቀው ቢሆንብኝ እንጂ፡፡ ለማንኛውም እግዚአብሔር ለሁሉም እውነቱን የሚገልጽበት፣ ኃያል ክንዱ የሚነሳበት ዘመን ላይ ቆመናልና ምርት እና ግርዱ ሲለይ እናየዋለን፡፡ ጥርጊያው ከፊታችን ነው፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
ኤልያስ አንተን የሚያውቁህ በፍቅርህም ያጌጡ የተደነቁ ናቸው፡፡ እኛም ስለ አንተ ደግነት በሕይወት እንኖራለን፡፡ ሲራክ 48፡11

ከኢእመ የተሰጠ መልስ፦