ከኪዳናዊ ኃይለ ማርያም የደረሰን፡ ኹለተኛ እጦማርና ለዚያ እጦማር የተሰጠ ምላሽ።

ከኪዳናዊ ኃይለ-ማርያም የተላከ እጦማር፦

ተፈጸመ ትስብእት፡ በኢትዮጵያ ማርያም ድንግል!
በብሥራተ ቅዱስ ገብርኤል፡ ዜናዌ ቃል!
 

ኪዳናዊ ወንድሜ ኂሩተ-ወልድ!
    «እግዚአብሔር አብ፥ እግዚአብሔር ወልድ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡ አንድ የኾኑባት "ቅድስት ሥላሴ"፡ ድንግል ማርያም ናት!» የሚለውን፡ የተዋሕዶ ሃይማኖታችን መሠረትና ዓምድ በተመለከተ፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፦ “ኀበ ርኅራኄክሙ በዝኀ፥ ወኀበ አልቦቱ መሥፈርት፡ እለ ትሰመዩ፡ በስመ ብእሲት፡ ሥላሴ ዕደወ ምሕረት፡ ግናይ ለክሙ” ማለትም፡ “ቸርነታችሁ ከበዛና መሥፈሪያም ከሌለው ዘንድ፥ “ቅድስት” ተብላችሁ “በሴት ስም” የምትጠሩ፡ የይቅርታ ወንዶች ሥላሴ ሆይ! ለእናንተ፡ መገዛት ይገባል።” ሲል፡ ሥላሴ፡ “ቅድስት” ተብለው የሚጠሩት፡ ከቸርነታቸው ብዛት የተነሣ እንደኾነ የሚያስመስል በመኾኑ፡ እንዴት ይታያል? 
    በቸር ያገናኘን። 
ከናፍቆት ሰላምታ ጋር፦ ኃይለ-ማርያም።

ከኢእመ፡ የተሰጠ ምላሽ፦ 

ተፈጸመ ትስብእት፡ በኢትዮጵያ ማርያም ድንግል!
በብሥራተ ቅዱስ ገብርኤል፡ ዜናዌ ቃል!
 

ኪዳናዊ ወንድሜ ኃይለማርያም!       
    የጻድቁን የአባ ጊዮርጊስ፡ ዘጋሥጫን፡ የድርሰት ጥቅስ መነሻ በማድረግ፡ ስላቀረብኸው ቍም ነገራዊ ጥያቄህ እግዜር ይስጥልኝ!                  
    መምሰል፥ ወይም፡ ማስመሰል፡ ተደርጎም፡ የታየው፥ ሲደረግም፡ የሚታየው፡ መንፈስ በኾነውም፥ ሥጋን በለበሰውም፡ በኹለቱም ፍጡራን ዘንድ እንጂ፡ በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም። መምሰልም፥ ማስመሰልም፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ፈጽሞ የለም። በእርሱ ዘንድ፥ በጸጋውም ዘንድ እንኳ ያለው፡ "በእውን መኾን!" እና "በእውን ማኾን!" ብቻ ነው። ስለዚህ ነው፡ ራሱ እግዚአብሔር፡ "እኔ፡ እውነት ነኝ!" ያለው። እኛም፡ ወገኖቹ፡ "እግዚአብሔር እውነት ነው!" የምንለው። የዚህም እውነታ፡ "አዳም ኮነ፡ ከመ አሓዱ እምኔነ!" ማለትም፡ "አዳም፡ ከእኛ፡ እንደአንዱ ኾነ!"፣ ደግሞም፡ "ቃል፡ ሥጋ ኮነ!" ማለትም፡ "ቃል፡ ሥጋ ኾነ!" በማለቱ ተረጋግጦ ይታወቃል።  እውነት፥ መልካምና ሕይወት የኾነውን እግዚአብሔርን የመምሰል፥ ወይም፡ ሓሰት፥ ክፉና ሞት የኾነውን ሰይጣንን የመምሰል ፍላጎትን የመረጠውና ያደረገው፡ ራሱ ፍጡር ነው። ይህም፡ ሊኾን የቻለው፡ ይኸው ፍጡር፡ "እንደእግዚአብሔር እስከመኾን አልቆ ያበቃውን፥ ወይም፡ ሌላውን፡ ተቃራኒውን ወደመኾን ያዋረደውን የምርጫ ነጻነትንና ሥልጣንንም እንኳ፡ ከፈጣሪው ተሰጥቶት ስላገኘው ነው።  
    ስለዚህ፡ ጻድቁ ደራሲ፡ "እለ ትሰመዩ፡ በስመ ብእሲት፡ ሥላሴ ዕደወ ምሕረት!" ማለትም፡ «“ቅድስት” ተብላችሁ በሴት ስም የምትጠሩ፡ የይቅርታ ወንዶች ሥላሴ ሆይ!» ብለህ፡ በመልካም በተረጐምኸው አንቀጽ ውስጥ፡ "እለ ትሰመዩ፡ በስመ ብእሲት!" ማለትም፡ "በሴት ስም የምትጠሩ!" ሲል፡ ያች፡ "ብእሲት!"ያች "ሴት!" ያላት፡ ታዲያ ማናት? ቅድስት ድንግል ማርያም እኮ ናት። ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል፡ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ መሢሕን ስለመፅነሷ፡ ለቅድስት ድንግል ማርያም፡"ወይሰመይ፡ 'ወልደ እግዚአብሔር ልዑል!'" ማለትም፡ "'የእግዚአብሔር ልጅ' ተብሎም ይጠራል!" ሲል እንዳበሠራት ማለት ነው። 
    ጻድቁን ደራሲ ጨምሮ፡ በቀደሙትም፥ በዛሬዎቹም፡ ኪዳናውያንና ኪዳናውያት የኢትዮጵያ ልጆች ዘንድ፡ ጸንቶ የኖረው፥ ዛሬም ያለው፥ ወደፊትም ለዘለዓለም የሚቀጥለው፡ ይህ እምነት ነው።     
በቅድስት ሥላሴ ፍቅር፡ ደኅና ኹን! 
ኪዳናዊ ወንድምህ፡ ን.እ. ኤርምያስ።