የመስከረም ለቺሳ፡ ''ዩቶፕያ (Utopia)'' የሚለው፡ የሰር ቶማስ ሞር መጽሓፍ፡ ኢትዮጵያኛ የትርጉም ሥራና የምርምር ማስታወሻዎች።

ይድረስ፦ ለኪዳናውያትና ለኪዳናውያን የኢትዮጵያ ልጆች! ለሌሎቻችሁም፡ የምንባብ ታዳሚዎቻችን ኹሉ!

እኔ፡ ኪዳናዊ ወንድማችሁ፡ ንቡረ-እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ-ኢየሱስ፡ ኢትዮጵያዊ ሰላምታዬን፡ በያላችሁበት፡ በእግዚአብሔር ስም አቀርብላችኋለሁ!

"ለእንግሊዝ መንግሥታዊና ሃይማኖታዊ ተሓድሶ፡ ምክንያት የኾነው፡ የመካከለኛው ዘመን፡ የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥትና የሕዝቧ አኗኗር -  (ኢ) ዩቶፕያ - የትርጕም ሥራና የምርምር ማስታወሻዎች - እውነተኛው "ሕዳሴ" ወይም "ተሓድሶ"፡ ከምንታዌነት (Dualism)፡ ወደተዋሕዶ (Unity) የሚደረግ፡ ኹሉን አቀፍ ኅብረተሰባዊ የንስሓ ጕዞ መኾኑን የሚያሳይ፡ ተጨባጭ እና ታሪካዊ ማስረጃ" በሚል አርእስት፡ በኪዳናዊት መስከረም ለቺሣ ተደርሶ፡ በ፳፻፮ ዓመተ ምሕረት የታተመውንና በሥርጭት ላይ የሚገኘውን መጽሓፍ አነበብሁት።

በማንበቤ፡ እጅግ ደስ ብሎኝ፡ እግዚአብሔር አብ አባታችንን፥ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ መሢሕን የወለደች፡ እግዚአብሔር እም እናታችን ኢትዮጵያን ድንግል ማርያምንም አመሰገንሁ፤ የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያና ሊቀ ምሁር፥ ደራሲና ተርጓሚ የኾነችውን፡ ወጣቷን ኪዳናዊት መስከረምንም፡ ከልዩ ሙገሳ ጋር፡ "አበጀሽ!" ብዬ መረቅሁ።

ይህንኑ፡ "Utopia" የሚለውንና በኹለት ጥራዞች የተጠቃለለውን፡ የሰር ቶማስ ሞር መጽሓፍ፡ የእንግሊዝኛውን ቅጂ፡ በቅድሚያ፡ በኅዋ ሰሌዳችን ላይ፡ ለይፋ ምንባብ እናቀርበው ዘንድ፡ ኹለታችንም፡ በጉዳዩ ላይ ተወያይተንበት የተስማማንበትን ውሳኔ፡ በሥራ ላይ ባዋልንበት ጊዜ፡ የተወሳውን፡ አንድ ታላቅና ተዛማጅ ቍም ነገር፡ እዚህ ላይ ማውሳቱ አግባብ ይኾናል። ያም ቍም ነገር፡ ይኸው የእንግሊዝኛው ቅጂ፡ እግዚአብሔር የፈቀደው ቀን ሲደርስ፡ በእርሷው አማካይነት፡ ወደኢትዮጵያኛ ተተርጉሞ፡ ለሕዝባዊ ምንባብ እንደሚበቃ የተማመንበት፥ እርሷም፡ በልቧ፡ ለፈጣሪዋ የሰጠችው፡ የተስፋ ቃል ነበር።

አዎን! ያ የተስፋ ቃል፡ እነሆ፡ በግብር ተፈጽሞ ማየቴ፡ ከላይ ላወሳሁት፡ ለእኔ፡ ለደስታየ እጅግነት፡ ተጨማሪው ምክንያት ይህ መኾኑን እየገለጽሁ፡ እርሷንም፡ "ቸሩ ፈጣሪና እናት ኢትዮጵያ፡ እንኳን፡ የተስፋ ቃልሽን፡ እውን ለማድረግ አበቁሽ!" እያልሁ፡ አድናቆቴን አበረክትላታለሁ።

እንግዴህ፡ በቅድሚያ፡ ይህን መጽሓፍ ማንበብ፥ ቀጥሎ፡ አንብቦ፡ የእግዚአብሔርንና የኢትዮጵያን እውነት፡ በትክክል መረዳት፥ በመጨረሻ፡ በምንባቡ እርግጠኛ ፍሬያማነት፡ ራስን፡ ለእውነተኛው ኢትዮጵያዊነት ማብቃት፡ "ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያዊት ነኝ!" ለሚለውም ኾነ፥ ለማይለው፡ ለእያንዳንዱ ወንድ እና ለእያንዳንዷ ሴት፡ የተፈጥሮም፥ የሃይማኖትም፡ ሰብኣዊ  ግዳጅ መኾኑን፡ ኹላችሁም አውቃችሁት፡ የየበኩላችሁን ተገቢ ድርሻ፡ በሰዓቱ ትከውኑ ዘንድ አሳስባችኋለሁ።

እኔም፡ ይህን መልእክት፡ ለእያንዳንዳችሁ፡ በነፍስ ወከፍ፡ በአክብሮትና  በትሕትና፥ በፍቅርና በሰላም፥ ይኸው ማስተላለፌ፡ ድርሻዬ የኾነውን፡ ይህንኑ ተልእኮዬን መወጣቴ መኾኑን እንደምትገነዘቡልኝ አምናለሁ።