የምትናገሩት፡ ስለየትኛዋ “ኢትዮጵያ’ እንደኾነ ልትገልጽልን ይቻላችኻል?
ስለ“ኢትዮጵያ” የሚቀርበው መልእክት፡ ሰው-ሠራሽ ከኾነችውና ስለኾነችው፡ ወይም ዓለማውያን የታሪክ ጸሓፊዎችና ምሁራን፡ እንደዚያች አስመስለው፡ ካቀረቡዋትና ስላቀረቧት፡ ወይም በዛሬው ኹኔታ፡ በገሃድ እንደሚታየው፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፡ በሥጋውያን የሥነ መንግሥት ፈሊጠኞች (Politicians) ከተፈጠረችውና ስለተፈጠረችው፡ “አስመሳይቱ ኢትዮጵያ”፡ አይደለም።
የምንናገረው፡ ይልቅስ፡ እግዚአብሔር ከሠራት፡ ጥንታዊና ኪዳናዊት፤ ሕያውትም ከኾነችውና ስለኾነችው፡ ስለእውነተኛይቱ ኢትዮጵያ ነው። እርሷም፡ ባህልና ቅርስ ባላቸው፡ በሠለጠኑት የዓለም አገሮች፡ ማለትም፡ በጥንታውያኑም፤ በማእከላውያኑም፤ በዘመናውያኑም ዘንድ፤ ደግሞ ሃይማኖተኞች በኾኑት የዓለም ሕዝቦች፡ ማለትም፡ በአይሁድና በክርስቲያኖች፤ በእስላሞችና በሌሎቹ እምነቶች ተከታዮች ዘንድ፤ እንዲሁም፡ መለኮታዊውን ወይም መለካዊውን፤ አምባገነናዊውን ወይም ሕዝባዊውን ፈለግ የተከተለ ሥርዓተ መንግሥትም ባላቸው ዘንድ ኹሉ፡ በዚህ ማንነቷ ታውቃ የኖረችውና ወደፊትም ስለምትኖረዋ ኢትዮጵያ ነው።
ስለጥንተ ፍጥረት የሚናገረው፡ ኦሪት ዘልደት (ዘፍጥረት) የተባለው፡ የመጽሓፍ ቅዱስ መክፈቻ፡ በተለይ ፪ኛው ምዕራፍ፤ “እግዚአብሔር አምላክ፡ በምሥራቅ በኩል፡በኤዶም፡ ገነትን አዘጋጀ፤ የፈጠረውንም ሰው በዚያ ሾመው፤ አኖረው። …ወንዝም፡ ገነትን ያጠጣ ዘንድ፡ ከፊትለፊቱ ይወጣ ነበረ፤ ከዚያም፡ ወደአራቱ የዓለም ማዕዘኖች ይከፈላል። የኹለተኛውም ወንዝ ስሙ፡ ‘ግዮን’ ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።” በሚለው መሠረት፡ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ታሪክ (ዝክረ ነገር)፡ ገና ከጅምሩ፡ ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ መጻፍና መናገር ይቻላል። እንግዲህ፡ የኹሉ መሠረት፡ ቋሚ፡ መዋቅር መጽሓፍ ቅዱስ እንደመኾኑ፡ ከላይ ለተጠቀሰው የ“ኢትዮጵያ” ማንነት፡ አስተማማኝ ማረጋገጫ ይኾነናል። ኾኖልናልም።