የኢትዮጵያ፡ የቃል ኪዳን ጸሎት።
እኛ፡ የኢትዮጵያ ልጆች፦
እግዚአብሔር፡ ለሰው ልጆች፣ ለወንዶቹም፥ ለሴቶቹም፣ የሰጣቸውን ቃል ኪዳናት፡ ጠብቆ በኖረው፡ በቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነታችን እናምናለን።
አምላካችን፡ ይህን የኢትዮጵያዊ እና የኢትዮጵያዊት ሕያው ሰውነት፡ በመጀመሪያው የፍጥረት ዘመን፡ በአዳምና ሔዋን ሥርዓተ ጋብቻ፡ በኪዳነ ልቦና መሠረተው፤
ከዚያም፡ በኖኅ ቀስተ ደመና፥ በመልከ ጼዴቅ ቍርባን እና በአብርሃም ግርዛት፡ ገንብቶ አሳደገው፤
በመካከለኛውም የሕግ ዘመን፡ በሙሴ ጽላትና በዳዊት ዙፋን አዋቅሮ፥ የኢትዮጵያዊቷን ንግሥት፡ የማክዳንና የእስራኤላዊዉን ንጉሥ፡ የሰሎሞንን የዘር ሓረጎች በማዋሓድ፡ በኪዳነ ኦሪት አከናወነው፤
በመጨረሻውም የሕይወት ዘመን፡ ከዚህ ምሉእ ትውልድ ከተገኘችው፡ ከእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም የተወለደው፡ እግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ ከእርሷ በነሣው ሥጋና ደም አጽንቶና ዘለዓለማዊዉን ዘውድ አቀዳጅቶ፡ በኪዳነ መንፈስ ቅዱስ ፈጸመው።
ኢትዮጵያ፡ እንዲህ በቀጠለው፡ በቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊው እና ኢትዮጵያዊቷ ሰውነት ገዝፋ፡ ቤተ ሕዝቧን፥ ቤተ ክህነቷን እና ቤተ ምልክናዋን፡ በምስጢረ-ተዋሕዶ፡ አንድ አድርጋ የኖረች፡ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደኾነች እናምናለን።
እርሱ፡ "ክርስቶስ" ተብሎ፡ እኛን፡ "ክርስቲያን" ያሰኘን፡ እግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ በቀደመው ዘመን፡ ለእርሱ፡ ለእግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ ምሳሌው ኾኖ በተገለጠው፡ በመልከ ጼዴቅ ኢትዮጵያዊነትና ሹመት፡ ከሴም፥ ከካም እና ከያፌት ዘሮች ተወልዶ፡ የዘለዓለም ካህናችንና ንጉሣችን እንደኾነ እናምናለን።
እርሷ፡ "ኢትዮጵያ" ተብላ፡ እኛን፡ "የኢትዮጵያ ልጆች" ያሰኘችን፡ እግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም፡ አሸናፊውን እግዚአብሔርን በመውለዷ፡ አማናዊቷ የሕይወት ዛፍ፥ የሕያዋን እናትና፥ ዘለዓለማዊቷ ታቦተ ጽዮን፥ የሰማይና የምድር ንግሥትም እንደኾነች እናምናለን።
በሦስቱ ታላላቅ ኅብረ-ቀለማት፡ በአረንጓዴ፥ ብጫና ቀይ ያሸበረቀው፡ የቀስተ ደመና ምልክት፡ በኖኅ አማካይነት፡ ከፈጣሪያችን እግዚአብሔር የተቀበልነው፡ የዘለዓለም ሰንደቅ ዓላማችን እንደኾነ እናምናለን።
ለእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም የተነገረው፡ "ኢትዮጵያ፡ እጆቿን፡ ወደእግዚአብሔር ታደርሳለች!" የሚለው ትንቢታዊ ቃል እና የቅዱሱ ኪዳን ፍጻሜ ለኾነው፡ ለእግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ የተነገረው፡ "የይሁዳው ነገድ አንበሳ፡ ድል ነሣ!" የሚለው መለኮታዊ ቃል፡ በቅዱሱ ኪዳን ሕዝብነታችን፡ ከአምላካችን እግዚአብሔር ያገኘነው፡ የዘለዓለም ማኅተማችን እንደኾነ እናምናለን።
በቅዱሱ ኪዳን ጸጋ፡ ከእግዚአብሔር፡ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት የመወለድን ክብር ስላገኘን፡ በዚህ ልጅነታችን፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች [ነጋሾች] እና ካህኖች [አገልጋዮች] እንደኾንን እናምናለን።
ይህን ልጅነታችንን፡ አጽንተን ለመጠበቅ፥ የመንግሥቱ ወራሽነታችንን፡ ለማረጋገጥና ንጹሕ አገልግሎታችንን ለመቀጠል፣ኃጢኣታችንን፡ ዘወትር በንስሓ እያጠራን፣ እግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ ከእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም የነሣውንም ሥጋና ደም እየተቀበልን፡ መኖር እንዳለብን እናምናለን።
የኢትዮጵያዊነት ሃይማኖታችን፡ በይፋ የሚገለጠውና ተለይቶ የሚታወቀው፡ ለእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም እና ለእግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ መሲሕ ባለን የተዋሓደ ፍቅር ኾነን፡ በምንፈጽመው፡ የኢትዮጵያዊነት ምግባራችን እንደኾነ እናምናለን።
የቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነታችንን፡ በየልቦናችን የጻፈው፣ ያስተማረንም፥ ጠብቀነው እንድንኖር ያደረገም፡ እንደቃል ኪዳኑ፡ እግዚአብሔር እንደኾነ እናምናለን። ለዘለዓለሙ፤ አሜን።