የኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ የ"አቡነ ዘበሰማያት"ን እና የ"ኦ ማርያም እምነ ዘበሰማያት"ን ጸሎታት፡ በተመለከተ፡ ለደረሱን፡ የነቀፌታ ትችቶችና መጠይቃውያን አስተያየቶች፡ የተሰጠ መልስ።

ይድረስ፦ ለአቶ ብንያም ምሕረት!
     ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ "ዮም ፍሥሓ ኮነ! በእንተ ርደተ መንፈስ ቅዱስ ላዕለ ኵላ ምድር፡ ዘኢትዮጵያ፡ መንግሥተ እግዚአብሔር!" እያለች፡ ሰላምታዋንና የእግዚአብሔር እውነት የኾነችውን፡ ኢትዮጵያዊት መልእክቷን፡ በእናትነት ፍቅር፡ እንዲህ በማስቀደም ታቀርብልዎታለች።
     በፌስቡክ መድረካችን ላይ፡ ስለጻፉልን ትችት፡ "እግዜር ይስጥልን!"
     እነዚህን የመሰሉት የነቀፌታ ትችቶችና መጠይቃውያን አስተያየቶች፡ አያሌ፡ የተደበቁ፡ የእግዚአብሔር እውነቶች እንዲከሠቱ ስለሚያደርጉ፥ ስለሚያስችሉም፡ በጣሙን ይጠቅሙናል፤ ያስፈልጉናልም። ምክንያቱም፡ አንዳንድ ጊዜ፡ የነቀፌታው ትችትና የመጠይቃዊው አስተያየት አቅራቢዎች፡ በምንሰጣቸው ምላሾች ረክተው፡ ወደእግዚአብሔር እውነት የማይመለሱ፡ አንገተ ደንዳናዎች፡ አልፎ አልፎ ቢገኙም እንኳ፡ ከአንባቢዎች መካከል፡ አውቀውና  ተረድተው፥ በንስሓም፡ ወደዚችው፡ ወደእግዚአብሔር እውነት ሊመለሱ የሚበቁ፡ ብዙ አስተዋዮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ነው፡ የነቀፌታ ትችቶቹና መጠይቃውያኑ አስተያየቶች፡ "ይጠቅሙናል፤ ያስፈልጉናልም!" ያልነው።