የኢትዮጵያ ልጆች፡ ለድንግል ማርያም የሚያቀርቡት፡ የሰላምታ ጸሎት።

እናታችንና መድኃኒታችን እግዝእተብሔር ማርያም ሆይ!

በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ፡ "ሰላም!" እንልሻለን።

በመንፈስሽ እና በነፍስሽ፣ በሥጋሽም፡ ድንግል ነሽ። በዚህ የንጽሕና ባሕርይሽ፡ የአሸናፊው የእግዚአብሔር እናት ነሽና፡ ይህ ሰላምታ፡ ለአንቺ ይገባል።

ማሕፀንሽ፡ የሕይወት ዛፍ ፍሬ የኾነውን፡ ቅዱሱን አዳም ስላስገኘ፣ አንቺ፡ ከሴቶች ኹሉ ተለይተሽ የተባረክሽ፡ ቅድስቲቱ ሔዋን ነሽ። ቀድሞ በነቢያት፡ "ኢትዮጵያ፡ እጆቿን፡ ወደእግዚአብሔር ታደርሳለች!"  የተባልሽ፥ እኛም፡ "እናታችን ጽዮን!" ስንልሽ የኖርን፡ በሰማይና በምድር ንግሥታችን ሆይ! ደስ ይበልሽ! እግዚአብሔር፡ አንቺን፡ የመዳናችን ምክንያት አድርጎ፡ ኪዳነ ምሕረቱን፡ ለዘለዓለም ፈጽሟልና፡ "ጸጋን የተመላሽ ሆይ! ብፅዕት ነሽ!" እያልን፡ ዘወትር እናመሰግንሻለን።

በአምላካችንና በሰላማችን፡ በእግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ አንቺ፡ ለእኛ፡ የአደራ እናታችን፥ እኛም፡ ለአንቺ፡ የአደራ ልጆችሽ ነንና፡ ከተወደደው ልጅሽ ያልተለየው እናትነትሽ፡ ከእኛም፡ ምንጊዜም፡ እንደማይለየን እናምናለን።

በዚህ ኹሉ፡ ለተደረገልን ቸርነት፡ ልዑል እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን።

ለዘለዓለሙ፤ አሜን።