የ፳፻፰ ዓ.ም. የደብረ ታቦር (ቡሔ) በዓል መልእክት።

የ፳፻፰ ዓ.ም. የደብረ ታቦር (ቡሔ) በዓል መልእክት።
እግዚአብሔር አብወእም፡
እንኳን፡
ልጃቸው ኢየሱስ መሲሕ፡ በግርማ መለኮቱ ተገልጾ የታየበትን፡
የደብረ ታቦርን በዓል፥
ዘንድሮም፡ በ፳፻፰ተኛው (በኹለት ሺ ስምንተኛው) ዓመተ ምሕረት፡
በያለንበት፡ በደኅና አድርሰው፡ በሰላም ለማክበር አበቁን!

+ + +

የደብረ ታቦር (ቡሔ) በዓል።

     ለእኛ፡ ለቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፡ ከዓበይት በዓሎቻችን፡ አንዱ የኾነው፡ በዓለ ደብረ ታቦር የሚውለው፡ በነሓሴ ፲፫ ቀን በመኾኑ፡ ለጾመ ፍልሰታ ሱባዔ፡ ልዩ ምዕራፍ ኾኖ፡ በታላቅ መንፈሳዊ ተመስጦና ማኅሌት ይከበራል።
     ይህ በዓል፡ መድኅናችን ኢየሱስ መሢሕ፡ በዐጸደ ሥጋ፡ ዐብረውት ከነበሩት ደቀ መዛሙርቱ መካከል፡ ጴጥሮስንና ያዕቆብን፥ ወንድሙንም ዮሓንስን፥ በዐጸደ ነፍስ ካሉት ባለሟሎቹ ደግሞ፡ ሙሴንና ኤልያስን፡ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በሚገኘው፡ "ታቦር" በተባለው፡ የወይራ ዛፍ ተራራ ላይ አምጥቶ፡ የባሕርይ አምላክነቱን በመግለጥ፡ ታማኞች አገልጋዮቹ፡ ሊያዩ የተመኙትን፡ እንዲያዩ፥ ሊሰሙ የተመኙትንም፡ እንዲሰሙ ያደረገበት ቸርነቱና ኃይሉ የሚዘከርበት ነው።
     ይህንም፡ እርሱ፡ ለሕዝቡ፡ በምሳሌ ያስተምራቸው የነበረው፡ ነቢዩ ኢሳይያስ፡ "እስመ እንዘ ይሬእዩ፡ ኢይሬእዩ። ወእንዘ ይሰምዑ፡ ኢይሰምዑ፤ ወኢይሌብዉ።"
     ማለትም፡ "እያዩ፡ ስለማያዩ፥ እየሰሙም፡ ስለማይሰሙ፣ ስለማያስተውሉም" ወገኖች፡ የተናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ መኾኑን፡ መድኃኒታችን፡ ለደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ፡ መልስ በመስጠት ያስረዳቸው ቃሉ፡ በሥርዓተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፡ ዘወትር ይወሳል።
     ይህም፡ "ወለክሙሰ፡ ብፁዓት አዕይንቲክሙ፡ እስመ ይሬእያ፤ ወዕዘኒክሙ፡ እስመ ይሰምዓ። አማን እብለክሙ! ከመ ብዙኃን ነቢያት ወጻድቃን፡ ፈተዉ ይርአዩ፡ ዘትሬእዩ፤ ወኢርእዩ። ወፈተዉ ይስምዑ፡ አንትሙ ዘትሰምዑ፤ ወኢሰምዑ።"
     ማለትም፡ "የእናንተ ግን፡ ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ፡ ብፁዓት ናቸው። እውነት እላችኋለሁ! ብዙዎች ነቢያትና እውነተኞች፡ እናንተ፡ ዛሬ የምታዩትን፡ ሊያዩ፡ እጅግ ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን፡ አላዩም። እናንተ፡ ዛሬ የምትሰሙትንም፡ ሊሰሙ፡ እጅግ ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን፡ አልሰሙም።" ሲል፡ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው ነው። (ማቴ. ፲፫፥ ፲፫-፲፯።) 

ሙሉውን ምንባብ ለመመልከት፡ እንደሚከተለው ይቀጥሉ!...

     የ''ቡሔ ዳቦ''፡ እግዚአብሔር እም ድንግል ማርያም፡ ''ገራህተ ሙሴ'' ማለትም፡ ''የሙሴ እርሻ'' ተብላ፥ አንድም፡ በጻድቍ የሙሴ እርሻ ብቻ ሳትወሰን፡ በመዝሙር፡ ''ወወሀብኮሙ ሲሳዮሙ፡ ለሕዝበ ኢትዮጵያ''፡ ማለትም፡ ''ለኢትዮጵያ (ለዓለም)ና ሕዝቦቿ፡ ምግባቸውን፡ አትረፍርፈህ ሰጠኻቸው!'' እንዳለ፥ እርሷ፡ እግዚአብሔር እም ድንግል ማርያም፡ ''ገራህተ ኢትዮጵያ'' ማለትም፡ ''የዓለሙ እርሻ'' ተብላ፡ ከእግዚአብሔር አብ፡ በመንፈስ ቅዱስ ግብር፡ አብባና አፍርታ፥ ፀንሳና ወልዳ ላስገኘችው፡ እርሱም በተራው፡ በዝናም አብቅሎና በፀሓይ አብስሎ፡ ፍጥረታተ-ዓለማቱን፡ አጥግቦ ለሚመግበውና አርክቶ ለሚያጠጣው፡ ለአማናዊው የቡሔ ኅብስት፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ ዘለዓለም፡ ምሳሌ ኾኖ የሚኖር ነው። (መዝ. ፸፫፥ ፲፫-፲፭፤ መዝ. ዳዊት፡ ንቡባ ከነትርጓሜው፤ ገጽ ፫፻፸፤ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፡ አ.አ. ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.።)

ሥዕሉን ለመመልከት፡ እንደሚከተለው ይቀጥሉ!...