ይድረስ፦ ለተከበሩና ለተወደዱ መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ

ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት።
ኢየሱስ መሢሕ ኢትዮጵያዊ፡
አንሶሰወ ገሃደ፤ ወአስተርአየ ከመ ሰብእ፤
በበሕቅ ልኅቀ፤ በሠላሳ ክረምት፡ በዮርዳኖስ ተጠምቀ።

ይድረስ፦ ለተከበሩና ለተወደዱ መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ።
     አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ።
  ከነቤተሰብዎና ከአገልግሎት ባልደረቦችዎ ጋር፡ እንደምን አሉ? አገራችን ኢትዮጵያ በኾነችው፡ በቅድስት እናቱ ድንግል ማርያም ምክንያት፡ እግዚአብሔር በምልዓት ባስገኘልን የቸርነት ልግሥናው፡ ለዘወትርና ለዘለዓለሙ ይክበር ይመስገን፡ እኔ ከኪዳናውያንና ኪዳናውያት ቤተሰቤና የአገልግሎት ባልደረቦቼ ጋር ደኅና ነኝ።
   ባለፈው ዓመት፡ በአዲስ አበባ ደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ዐፀደ ቤተ ክርስቲያን በነበረው ክህነታዊና ተአምራዊ የጉባኤ አገልግሎትዎ ላይ፡ ባለቤቴ፡ ኪዳናዊት እመቤት ራሔል ዘካርያስ፥ እንዲሁም፡ ከልጆቻችን መካከል፡ ኪዳናውያት እመቤታት ትምህርተ ኤርምያስና ስብከተ ኤርምያስ፥ ኪዳናዊ አበቤት ሰማዕተ ኤርምያስም ተገኝተው ስለነበረ፡ እርስዎ፡ በቅዱሱ ኪዳን የኢትዮጵያዊነት ሃይማኖታችን መሠረት ከሚሰጡት የምሥራች ትምህርትዎና ስብከትዎ፥ ይልቁንም ትንግርታዊ ከኾነው፡ ከምግባራዊው የንስሓና የፈውስ ተልእኮዎ፡ መንፈሳዊዉን ጸጋና በረከት ሊሳተፉ ችለው እንደነበረ ላስታውስዎ እወድዳለሁ።