ከአንድ፡ የፌስ ቡክ ዕድምተኛችን ለደረስን፡ አስተያተትና ጥያቄ፡ የተሰጠ ምላሽ።
ከዕድምተኛችን የደረሰን።
ይህ፡ "እግዚአብሔር" የሚለው ሓሳብ፡ ዘወትር፡ በልቤ እየተመላለሰ ሲያስቸግረኝ፡ በጽሑፍ አሠፈርሁት። ብዙ ሰዎች ወቀሱኝ፤ ብዙ ሰዎች አመሰገኑኝ። እናንት ግን፡ ስለዚህ ነገር የምታውቁት ነገር ካለ፡ ወቀሳም ቢኾን ልቀበል ዝግጁ ነኝና ያላችሁን ሓሳብ ጻፉልኝ። በቀጣይ፡ ሌላ፡ ልቤ ውስጥ ደጋግሞ እየመጣ፡ "ግለጠኝ" የሚል ሓሳብ አለኝ። ከእናንት ጋር ተመካክሬ፡ ለመግለጥ እሞክራለሁ። ዋጋ የሚያስከፍለኝ ቢኾንም፡ እርሷ እመቤቴ፡ ግለጥ ካለችኝ፡ እገልጠዋለሁ። አመሰግናለሁ።
''እግዚአብሔር'' ማለት፡ ምን ማለት ነው?
እግዚ ማለት እናት ማለት ነው (ወላዲተ አምላክ)፥
አብ ማለት አባት ማለት ነው (ትልቅ ኃያል) እና
ሔር ማለት ልጅ ማለት ነው (ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ)።
ይህን እና ሌሎች ሃይማኖት ውስጥ የማላገኛቸው፡ ብዙ እውነታዎችን፡ በሕልሜ፡ ወይም፡ በማሰላሰል ይነግረኛል። አብዛኛው የተረዳሁት ነገር ደግሞ፡ በእናንተ አስተምህሮት ላይ፡ ሙሉ በሙሉ ሲገለጽ ሳይ ነው፡ የምሰማው እውነት መኾኑ የገባኝ። እናም፡ እባካችሁ፡ ብዙ መግለጥ ያለብኝ ነገር ስላለ፡ መልእክቴ እንደደረሳችሁ ጻፉልኝ። ክብር፡ ለኢትዮጵያ እናት፡ ለወላዲተ አምላክ ይኹን። አሜን።
ከኢእመ የተሰጠ መልስ።
ይድረስ፦ ለተወደዱና ለተከበሩ …….
እመቤታችንን በሚመለከት፡ ስላደረሱን መልእክት፡ እግዚአብሔር ይስጥልን።
መልእክትዎን የተቀበልነውና የተረዳነው፡ በመንፈስ ቅዱስ ተነሣሥተውና ተቃኝተው የጻፉት እንደኾነ ነው። ይህን የሚያረጋግጠው፡ ሌላኛው ማስረጃ፡ መልእክትዎን የጻፉልንና ያደረሱን፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት አማካይነት፡ ስለድንግል ማርያም፡ ቅድስት ሥላሴና እግዚአብሔራዊ ምንነትና ማንነት፡ በይፋና በገሃድ፡ በአዋጅ ቃል የተላለፈውን መለኮታዊ ቃል፡ ተከትሎና መሠረት አድርጐ በመኾኑ ነው። እርስዎም፡ «ይህን እና ሌሎች ሃይማኖት ውስጥ የማላገኛቸው፡ ብዙ እውነታዎችን፡ በሕልሜ፡ ወይም፡ በማሰላሰል ይነግረኛል። አብዛኛው የተረዳሁት ነገር ደግሞ፡ "በእናንተ አስተምህሮት ላይ፡ ሙሉ በሙሉ ሲገለጽ ሳይ ነው፡ የምሰማው እውነት መኾኑ የገባኝ"።» ያሉት፡ ለእዚህ ምስክር ነው።
ስለዚህ፡ አኹንም፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡ በሥነ ፍጥረት ዓለማቱ በምልዓት ስላለች፡ ሕያዊትና ዘለዓለማዊት አርያሙ፡ እግዝእትነ ማርያም፡ የሚያሳስብዎትን እውነትና እውቀት፡ በእውነተኛ የጾምና የጸሎት ሃይማኖታዊ ምግባር ኾነው፡ መልእክቱን ሊቀበሉና ምሥራቹን ሊያስተላልፉ ይገባል።
"እግዚአብሔር" ስለሚለው፡ መለኮታዊ ቃል ትርጒም፡ በእኛ በኩል የምናሳውቅዎ፡ ይህንን ነው፦
"እግዚአብሔር" የሚለው፡ "ቅድስት ሥላሴ" እንደምንለው፡ የፈጣሪ፡ የአንድነቱና የሦስትነቱ ምስጢር መገለጫና መጠሪያ ስም ነው። "ቅድስት" የሚለው፡ የሥላሴ፡ ማለትም፡ የእግዚአብሔር አብ፥ የእግዚአብሔር ወልድና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡ የአንድነት ስማቸው ሲኾን፡ «"ቅድስት" የተባለች አንድነታቸውም፡ እግዚአብሔር እም፡ ድንግል ማርያም ናት።» (ሉቃ. ፩፥ ፴፭።)
ስለዚህ፡ "እግዚአብሔር" ማለትም፡ "የሥነ ፍጥረቱ ፈጣሪና ገዥ፥ ባለቤትና መጋቢ"፡ የሚለው፡ የአንድነቱ መገለጫና መታወቂያ፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ስትኾን፥ ሦስትነቱ ደግሞ፡ "እግዚእ" ማለት፡ ፈጣሪ፡ ወይም፡ ገዥ ሲኾን፡ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስን ይወክላል፥ "አብ" ማለት አባት ማለት ሲኾን፡ እግዚአብሔር አብን ይወክላል፥ "ሔር" ማለት ቸር ማለት ሲኾን፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ይወክላል።
በቅድስት ሥላሴ ፍቅር፡ ደኅና ይቆዩን።
የኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮች።