“ኢትዮጵያ እግዚአብሔር መንግሥት”፡ “ኦርቶዶክስ” ወይም፡ “ኮፕቲክ” የሚለውን መጠሪያ ስያሜ አለመጠቀሟ ለምንድን ነው?
በቅዱሱ ኪዳን ጸንታ የኖረችው፡ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ፡ ቀደም ብላ፡ ከኪዳነ ልቦና ወደኪዳነ ኦሪት ተሸጋግራ ከቆየችበት እምነቷ፡ በምሥጢረ ጥምቀት፡ ለክርስትና እምነት፡ ማለትም፡ ለኪዳነ መንፈስ ቅዱስ የበቃችው፡ ከክርስቶስ ልደት በኃላ፡ አርባ ዓመት ሳይሞላ እንደኾነ ይታወቃል። ይኹን እንጂ፡ ቤተ ክህነቷ፡ “ቤተ ክርስቲያን” ተብላ፡ እንደአዲስ የተቋቋመችው፡ ክርስቶስ በተወለደ፡ በአራተኛው ምዕት ዓመት እንደኾነ የሚያስመስል፡ የሓሰት ይትበሃል፡ በግብፃውያን አማካኝነት ሠርጎ እንዲገባ ተደርጓል። የዚሁ፡ የባዕዳኑ ይትበሃል ጠንቀኛ ውጤቶች የኾኑትን፡ “Coptic” (ኮፕቲክ) እና “Orthodox” (ኦርቶዶክስ) የተባሉትን፡ የግብጽና የግሪክ የሃይማኖት መለያ የኾኑትን ቃላት፡ በተቀጽላነት በመጨመር፡ “የኢትዮጵያ Coptic ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን” ወይም “የኢትዮጵያ Orthodox ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” የሚለው አጠራር ጸንቶ እንዲቀጥል ተደርጓል።
ይህ አጠራር፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክህነት፡ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ያላትን የቀዳሚነት ደረጃ በመሻር፡ “የግብጽ ወይም፡ የግሪክ፡ ከኹለቱ የአንደኛቸው፡ ቅኝ” መኾኗን ለማረጋገጥና ባዕድ የኾነውን ዓላማ፡ በቀላሉ ከግብ ለማድረስ እንዲያመች፡ ኾን ተብሎ በዕቅድ የተቀነባበረ መኾኑ ግልጽ ነው።
የነዚኽ ባዕዳን ቃላት፡ በስሟ መካከል መዘነቅ (መደባለቅ)፡ በቀላሉና በአጭሩ ሊነቀሉ የማይችሉ፡ ኹለት ዓበይት ጠንቆችን አስከትሏል።
፩ኛ. እግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ጥንት፡ በአበው ልቦና መሥርቷትና በመካከሉ፡ በኪዳነ ኦሪት አጽንቷት፥ በመጨረሻ፡ በኪዳነ መንፈስ ቅዱስ የፈጸማትን፥ ከዚህ የተነሣም፡ በዓለም ላይ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት ኹሉ ቀድማና ለብቻዋ እጅግ ጥንታዊት ኾና የኖረችውን፥ አንዲት የኾነችውን፡ የኢትዮጵያን ቤተ ክህነት፡ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ባለው፡ በአራተኛው ምዕት ዓመት ግድም፡ በዚኹ ስም ተለይተው በታወቁት፡ በግሪክ፡ ወይም በኮፕት (በግብፅ) ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተመሥርታ እንደተቋቋመች ማስመሰሉ ነው።
፪ኛ. ኹለተኛውና አስከፊ የኾነው ጠንቅ ደግሞ፡ “ኦርቶዶክስ” ከሚለው ቃል የተነሣ፡ ኢትዮጵያ፡ በነገረ መለኮት ሃይማኖታዊ አቋሟ፡ ከካቶሊኮች ጋር ተመሳሳይ በኾነው፡ በግሪኮች ኦርቶዶክሳዊ እምነት ላይ እንተመሠረተች ያስቆጠራት መኾኑ ነው። የኃላ ኃላ ግን፡ ኢትዮጵያውያን፡ “ተዋሕዶ” የሚለውን የግእዝ ቃል፡ ቢቸግራቸው፡ በመጠሪያ ስሟ መካከል ተጨማሪ እንዲኾን አድርገው፡ “የኢትዮጵያ Orthodox ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” የሚለውን አጠራር የሰጡት፡ “ሃይማኖታቸው የቆመበትን ጥንታዊ መሠረት፡ ለጊዜው፡ ከእነዚሁ ጠንቆች ለማዳን ይቻል ይኾናል፤” ብለው በማሰብ መኾኑን፡ መገንዘብ ያስፈልጋል።
እንግዲህ፡ ኢትዮጵያ፡ የባዕዳን የኾነውን በማይከተለው፡ በራሷ ባህል፡ መለያየትና መከፋፈል ሳይኖርባት፡ “ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር መንግሥት” በሚለው አቋሟ፡ አንዲት ስለኾነች፡ ሌላ ተጨማሪ መለያ ስያሜ ከቶ አያስፈልጋትም።