‘መንግሥት’ ምንድን ነው?
''መንግሥት''ማ፡ ግዙፉና ረቂቁ ዓለማት፡ በውስጣቸውም፡ በየወገኑና በየፊናው፡ በሕያውነት ያሉት፡ ፳፪ቱ (ኻያ ኹለቱ)፡ ሥነ-ፍጥረታት፡ ገና፡ የመፈጠር ክብርና ጸጋ፣ ብዕልና ሀብት፣ ዕድልና ጥዋ፡ ሳይደርሳቸውና ሳያገኙ፡ በባሕርይ ሕይወቱና ህልውናው፡ መንፈስ የኾነውና በዚህ አኗኗሩም፡ ''ምሉዕ በኵለሄ''፡ ማለትም፡ ''በኹሉ ለመላው'' አንዱ መለኮት፡ ልክ ለሰው ልጆች በነፍስ ወከፍ እንደተሰጠችውና የእግዚአብሔርን መልክ ነሥታ እንደተፈጠረችው፡ ''እስትንፋስ''፡ ይህችዪቱ መንግሥትም፡ የባሕርይው ማንነት ናት።
እንዲህም እንደመኾኗ፡ በኹሉ የመላው፡ መለኮት፤ ሥነ-ፍጥረትን፡ ከማሥረጹና ፈጥሮ፡ ''እምኀበ አልቦ ኀበቦ''፣ ''እምኀበ ኢምንት ኀበምንት''፡ ማለትም፡ ''ካለመኖር ወደመኖር'' በሕያውነት፡ ከማምጣቱና ከማሸጋገሩ አስቀድሞ፡ የባሕርይው ህልውናው በኾነችው፡ በአንዲት መንግሥቱ፡ ሰፍኖና ሠልጥኖ በንጉሥነትና በእግዚእና ማለትም፡ በጌትነት አለ። ይህች፡ ጥንተ-መነሻ የሌላት፡ የመለኮት፡ የባሕርይው፡ ገንዘቡና ጥሪቱ የኾነችው፡ መንግሥቱም፡ እግዚአብሔር፡ ሥነ-ፍጥረቱን ባስገኘበት ቅጽበትና አፍታ፡ በፍጥረተ-ዓለሙ አካልና ባሕርይ፡ ለራሱ ለፍጡሩ ገሃድና ይፋ ወጥታ የታየችና የተገለጠች ናት፤ አልፎም፡ ይህው ፍጡሩ፡ በፈጣሪው ካህንነት (አገልጋይነት) እየተገለገለባት ያለች፡ ደጊቱ እናት (መኖሪያ)፣ ተገን (ከለላ)ና ጽዮን፡ ማለትም፡ መጠጊያ ናት፤ መንግሥት፡ በዚህም ሳታበቃ፡ እንደአምላካዊው ቃል፡ '''እምነ ጽዮን!' ይብል ሰብእ፥ ወብእሲ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ተወልደ በውስቴታ! ወውእቱ፡ ልዑል ሣረራ!'' ማለትም፡ '''ሰው፡ 'እናታችን ጽዮን!' ይላል፥ በውስጧም፡ ሰው (ኢየሱስ ክርስቶስ) ተወለደ! እርሱ፡ ራሱም፡ ልዑል መሠረታት!'' ተብላ፡ ህልውናዋን በድንግል ማርያምና በኢየሱስ ክርስቶስ፡ በዘለዓለማዊነት የቀጠለችዋ ናታ። (መዝ. ምዕ. ፹፮፣ ቍ. ፭።)