ሥርዓተ-ተክሊል፡ ዘቅድስት፥ ወዘሓኪም። Sacrament of Matrimony for Qdst and Zehakim.
ይድረስ፦ ለተወደዳችሁ፡ የክህነት ባልደረቦቼ፡ ኪዳናውያት እኅቶቼና ኪዳናውያን ወንድሞቼ!
በእግዚአብሔራዊው ሰላማችን ኢየሱስ መሲሕ የጾሙ መታሰብያ ሓሤት ተመልተን፡ ኹላችንም፡ በእያለንበት፡ ከነቤተሰቦቻችን፡ በመልካሙ ሕይወታችን እንደምንገኝ፣ ለዚህ ቸርነቱም፡ ፈጣሪያችንን፡ ከነእናቱ፡ ያለማቋረጥ እንደምናመሰግን አምናለሁ።
ይህን እ-ጦማር የጻፍሁላችሁ፡ በዚሁ፡ በጾሙ መታሰብያ ጊዜ፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ አንድ እንግዳ ተአምር ደርሶ ስለታየ፡ የእርሱን፡ የምሥራች ዜና ላሰማችሁ ብዬ ነው፤ እርሱም፡ እነሆ፦
በዘንድሮው፡ የየካቲት ፲፮ ቀን፥ ፳፻፱ ዓ.ም. ዓመታዊ የኪዳነ-ምሕረት በዓላችን ዕለት፡ የቅዱሱ ኪዳናችን ባለቤቶች፡ እግዚአብሔር አብ፣ እግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም እና ልጇ ወዳጇ፡ እግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስነታቸው፡ የስማቸው መጠሪያና ርስት-ጉልታቸው በኾነችው፡ በዚች፡ በኢትዮጵያ ምድራቸው፡ በመካከላችን ተገኝተው፡ አንድ፡ ሌላ፣ አዲስ፣ ቃና ዘገሊላዊ ተአምራቸውን፡ እንደገና ፈጽመዋል።
ይህ የኾነበትንም ምክንያት ልግለጥላችሁ፦
ዕለቱ፡ በእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም ምሥዋዐ መድኃኒትነቷ እና በልጇ በወዳጇ፡ በእግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ የሰላመ-መስቀሉ ቤዛነት፡ ለፍጥረታተ ዓለማታቸው ያስገኙት፡ ዘለዓለማዊውና መለኮታዊው ምሕረታቸው፡ በቅዱሱ ኪዳን መጽናቱ፡ የተረጋገጠ ስለመኾኑ የሚከበርበት ዓመታዊው በዓላችን በመኾኑ ብቻ አይደለም፤
ነገር ግን፡ ሙሽራዪቱ፡ እንደማናችንም የሰው ፍጡሮች፡ የዘለዓለም አባት እናቷ የኾኑት፡ ፈጣሪዎቿ፣ ቅድስት ሥላሴ፡ በመልካቸው እና "ከእኛ እንደአንዳችን ኾንሽ!" ብለው፡ በሰውነት አካልና ባሕርይ፥ በሴትነትም ጾታ፡ በማሕፀን ፈጥረው፡ ወደዚህ ዓለም ልከዋት፡ የተወለደችበት ቀን፡ ይኸው የካቲት ፲፮ ቀን በመኾኑ እና
ከዚህ የተነሣ፡ ቀደም ብሎ፡ በሰኔ ፲፮ ቀን፥ ፳፻፰ ዓመተ ምሕረት፡ በቍጥር ፲፬/፳፻፰፡ በታወጀው በመለኮታዊው ዐዋጅ ተገልጦ እንደተነገረው፡ በእግዚአብሔር እውነትና በመንፈስ ቅዱስ አምልኮዋ፤ በዚያ በዓለ-መንፈስ ቅዱስ ዕለት፡ ራሷን፡ በቅዱሱ ቍርባን፡ እንደገና የወለደችው፡ ሙሽሪቷ ዐጸደ-ማርያም፡ ዛሬ ደግሞ፡ ራሷን፡ ለኪዳነ-አዳም ወሔዋን ጋብቻ ለማብቃት የመረጠችው ዕለት፡ ይኸው፡ የልደቷ ቀን፡ የካቲት ፲፮ ቀን በመኾኑ፣
ደግሞም፡ ጋብቻው፡ በዚሁ ምክንያት፣ በዚሁ ቀን እንዲፈጸም፡ ተአምራዊ በኾነው፡ በመንፈስ ቅዱስ አሳሳቢነት፡ ይኸው ቀን፡ በእርሷ ቤተሰብ ዘንድ ብቻ ሳይኾን፡ በሙሽራውም ዘንድ፡ ቀደም ብሎ፡ ስለተመረጠ ጭምር ነው።
በዚህ፡ መለኮታዊ የተአምር በዓል ላይ፡ በአካለ-ሥጋ ጭምር ተገኝተን፡ የሓሤቱ ተካፋዮች ለመኾን የታደልነው፡ እኛ፡ እዚህ፡ በቅርብ ያለነው፡ ኪዳናውያንና ኪዳናውያት የኢትዮጵያ ልጆች ብቻ ሳንኾን፡ በሩቅ ያላችሁት፡ እናንተም ጭምር፡ በአካለ-መንፈስ የተገኛችሁ በመኾናችሁ፡ በዚህ ረገድ፡ በዚሁ፡ በመለኮታዊው የተአምር በዓል፡ የኾነውን ኹሉ ታውቁትና የሓሤቱ ተካፋዮች ትኾኑ ዘንድ፡ በበዓሉ ዕለት ስለተፈጸመው፡ ስለዚሁ ተአምር፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት የተዘጋጀውን፡ አንድ ጥራዝ ጽሑፍ ዕትም እና አንድ ሥዕላዊ መጽሔትን፡ ከዚህ የደብዳቤዬ ማስታወሻ ጋር ልኬላችኋለሁና፡ ኹላችሁም፡ እንድትመለከቱት ይኹን።
የካቲት ፳፩ ቀን፣ ፳፻፱ ዓ. ም.
በቅዱሱ ኪዳን ወንድማችሁና የክህነት [የአገልግሎት] ባልደረባችሁ፦
ኪዳናዊ ኤርምያስ ከበደ ወልደ-ኢየሱስ [ንቡረ-እድ፡ ዘአኵስም ጽዮን።]
መልእክቱን በሙሉ ለመከታተል፡ እንደሚከተለው ይቀጥሉ!...
ሥዕላዊ መጽሔቱን ለመመልከት፡ እንደሚከተለው ይቀጥሉ!...