ስለታቦተ ጽዮን የተላለፈ፡ የእግዚአብሔር መልእክት።

ከኪዳናዊ ኃይለ ማርያም፡ በእንግሊዝኛ ተጽፎ የደረሰን መልእክት።

ከኪዳናዊ ንቡረ-እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ-ኢየሱስ የተሰጠ ሓተታ።

ዮም ፍሥሓ ኮነ!
በእንተ ርደተ መንፈስ ቅዱስ ላዕለ ሓዋርያት፡
በጽርሓ ጽዮን ቅድስት!

ይድረስ፦ ለኪዳናዊ ኃይለ ማርያም!
     ኢትዮጵያዊዉን የፍቅርና የናፍቆት ሰላምታዬን፡ በቅድስት ሥላሴ ስም ሳቀርብልህ፡ በያለንበት የሚጠብቀንንና የሚመራንን መንፈስ ቅዱስን እያመሰገንሁ ነው።
     ከሰባቱ ቅዱሳት ኪዳናት መካከል፡ ለእስራኤል ልጆች ተሰጥተው፡ እነርሱ ግን፡ አክብረው ሊፈጽሟቸው ባለመቻላቸው፡ ወደእኛ ወደኢትዮጵያ ልጆች ተመልሰው መጥተውና በአደራ ተጠብቀው፥ በትክክለኛው መለኮታዊ ምግባርም ላይ ውለው፡ ሲሠራባቸው ከቆዩ በኋላ፡ ትንቢታዊው ጊዜ ሲደርስ፡ በእኒሁ የኢትዮጵያ ልጆች፡ ለፍጹሙ ፍሬ የበቁት ኪዳነ ሙሴና ኪዳነ ዳዊት የተገለጡበትን፡ የ"ታቦተ ጽዮን"ን እና የ"ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ"ን ትእምርታት ዝክረ ነገር በሚመለከት፡ ወደአንተ በደረሰ የመንፈስ ቅዱስ እውቀት፡ በእንግሊዝኛ ተጽፎ፡ በፌስቡክ መድረክ ላይ የተከሠተ ድርሰትህን ልከህልኝ አገኘሁት፤ በልዩ የትፍሥሕት ስሜትም ኾኜ ተመለከትሁት፤ እግዜር ይስጥልኝ!