ስለኪዳናውያን አንተታና፥ ስለኪዳናውያት አንቺታ።

ዮም ፍሥሓ ኮነ! በእንተ ርደተ መንፈስ ቅዱስ፡ ላዕለ ሓዋርያት፡ በጽርሓ ጽዮን ቅድስት!   

ይድረስ፦  ለኪዳናውያንና ለኪዳናውያት የኢትዮጵያ ልጆች! በያላችሁበት!  

ከኪዳናዊ ወንድማችሁ፡ ከንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ-ኢየሱስ እና  ከኪዳናዊት እኅታችሁ፡ ከእመቤት ራሔል ዘካርያስ። የእግዚአብሔር መንግሥት ኢትዮጵያ አገልጋዮች።  

"እንደምን አላችሁ?" እያልን፡ ኪዳናዊ የኾነ፡ ኢትዮጵያዊ ሰላምታችንን እናቀርብላችኋለን። እግዚአብሔር ይመስገን፡ በቅድስት እናቱ፡ ድንግል ማርያም፡ ረድኤትና በረከት፡ እኛ ደህና ነን።

እያንዳንዳችሁ እናንተ፡ በቅዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በፍጹም ብቅዓት፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ኢትዮጵያ፡ እውነተኞች ኪዳናውያት እና ኪዳናውያን ልጆች፥ ነጋሢዎችና ካህናት (አገልጋዮች) መኾናችሁን፡ በቃል ኪዳን የምስክር ቃላችሁና በምትኖሩት ሕይወት፡ ለእየራሳችሁና ለፈጣሪያችሁ፥ ለእኛ፡ ለመሰሎቻችሁና ለሰውም ኹሉ አሳውቃችኋል። አኹን፡ ይህን እውነታ የምታረጋግጡበት፡ አንድ ቀላል ፈተና፡ እነሆ ቀርቦላችኋል።  

ይህን የቅደም ተከተል፡ ቀላል ፈተና፡ አልፋችሁና አሸንፋችሁ፡ የድሉን አክሊል መቀዳጀታችሁን የምታስመሰክሩበትን ሃይማኖታዊ ምግባር መፈጸማችሁን፡ ለእየራሳችሁና ለፈጣሪያችሁ፥ ለሰውም የምታሳዩት፡ እናንተው ናችሁ።

እኛ፡ ይህን ጥያቄ፡ ለእናንተ የመልስ ውሳኔ በማቅረባችን፡ የበኩላችንን ኪዳናዊ ኃላፊነት፡ በፈቃዳችን መወጣታችን፥ ግዳጃችንንም መፈጸማችን መኾኑን፡ ልናሳውቃችሁ እንወድዳለን። የጥያቄውን ትክክለኛ መልስ በመስጠቱ ረገድ፡ የየበኩላችሁን ኪዳናዊ ኃላፊነት፡ በየፈቃዳችሁ፡ የመወጣቱና በተግባር ላይ የማዋሉ ግዳጅ ደግሞ፡ የእናንተ ድርሻ ይኾናል።