የኢትዮጵያ: የሃይማኖት ጸሎት።

እኛ፡ የኢትዮጵያ ልጆች፦

አንድ አምላክ በሚኾን፡ በአሸናፊው እግዚአብሔር  እናምናለን። 

እርሱም፡ ኹሉን የያዘው፣ ሰማይንና ምድርን፥ የሚታየውንና የማይታየውንም የፈጠረው ነው።

አንድ አምላክ የኾነው፡ አሸናፊው እግዚአብሔር፡ ይህን አንድነቱን፡ እርሱ በሠራው፡ በመለኮታዊው የጋብቻ ሥርዓት፡ በእግዚአብሔር አብእም ኹለትነት፡ ፍጹም እንዳደረገው እናምናለን።

የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት፡ የአሸናፊው እግዚአብሔር ቅድስት ሥላሴ ዙፋንና የእግዚአብሔር መንግሥት ኢትዮጵያ በኾነችው፡ በእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም፡ የተዋሕዶ አኗኗርና አካል እንደተገለጠ እናምናለን።

ዓለም ሳይፈጠር፡ ከእርሱ ጋራ በነበረ፥ አንድ የእግዚአብሔር አብእም ልጅ፥ አንድ ጌታ በሚኾን፡ በእግዚአብሔር ወልድም እናምናለን።

እርሱም፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፥ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፥ የተወለደ እንጂ፡ ያልተፈጠረ፥ በመለኮቱ፡ ከእግዚአብሔር አብእም ጋራ የሚተካከል፥ ኢየሱስ መሲሕ ነው። 

በእርሱም፡ ኹሉ ኾነ። በሰማይ ካለው፥ በምድርም ካለው፡ ያለእርሱ፡ ምንም ምን የኾነ የለም።

ስለእኛ ስለሰዎች፥ ስለሰላማችን፡ ከሰማይ ወረደ። እግዚአብሔር እም፡ ስለመዳናችን፡ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቀዳሚ ግብር ከተዋሓደቻት፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም፡ ከሥጋዋ፡ ሥጋን፥ ከነፍሷም፡ ነፍስን፣ ከመንፈሷም፡ መንፈስን ነሥቶ፡ ፍጹም ሰውን ኾነ።

በጴንጤናዊው ጲላጦስ ዘመን፡ ስለእኛ መከራን ተቀበለ። ተሰቀለ። ሞተ። ተቀበረ።

"ኃጢኣት" የተባለው፡ የሓሰት፣  የክፋትና የሞት፣ የመቃብር-መበስበስም አባት የኾነውን ዲያብሎስን፡ ድል አደረገው።

በሦስተኛውም ቀን፡ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ።

በክብር በምስጋና ወደሰማይ ዐረገ።

በእግዚአብሔር አባቱና እናቱም ቀኝ፡ በእኩያ ዙፋኑ ተቀመጠ።

ለደቀ-መዛሙርቱ የሰጣቸውን የተስፋ ቃሉን በመፈጸም፣  በመንፈስ ቅዱስ ህልውናው ተመልሶ መጣ። የመጀመሪያዋን መንፈሳዊት የትንሣኤ ሕይወትም፡ ለብፁዓንና ለብፁዓት፣ ለቅዱሳትና ለቅዱሳን የኢትዮጵያ ልጆች፡ አቀዳጀ።

በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድም፡ በትንሣኤ አካሉና በክብሩ ምስጋና፡ ለመላው ከሃዲ፡ የዓለማቱ ኹሉ ፍጥረት፡ ዳግመኛ ይመለሳል።

"ኢትዮጵያ" ለተባለችው መንግሥቱም፡ ፍጻሜ የላትም።

በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም እናምናለን።

እርሱም፡ ሕይወትን የሚሰጠው እና ከእግዚአብሔር አብእም የሠረፀው፤ በእግዚአብሔር አብእም በስተግራ ባለው፡ የእኩያ ዙፋኑ የተቀመጠው፣ ከእግዚአብሔር አብእም እና ከእግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ ጋር፡ የምንሰግድለት፣ የምናመሰግነውም፡ ቅዱሱ የእውነት መንፈስ ነው። 

በነቢያት ዐድሮ የተናገረው እና በሓዋርያት ላይ የወረደው፣ በእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም፡ የማዳኗ ምሥዋዕነት እና በእግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ የመሰቀሉ ሰላም ቤዛነት፡ ዓለሙን፡ በጸጋው የሞላው፡ እርሱ ነው።

እግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ፡ ጥንት፡ በቀደሙት ሰዎች ኪዳነ ልቦና በመሠረታት፡ በአንዲት ቅድስት ኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት እናምናለን።

እርሷም፡ በነቢያት ቃል ያጸናት እና በሓዋርያት ጕባኤ የፈጸማት፥ ካህናት፡ ከእግዝእተብሔር እም፡ ድንግል ማርያም የነሣውን፡ የእርሱን፡ የእግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕን፡ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም፡ ለመሥዋዕትነት የሚያቀርቡባት፥ ኪዳናውያንና ኪዳናውያት የኢትዮጵያ ልጆችም፡ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋዎች የሚቀበሉባት ናት።

ኃጢኣት በሚሰረይባት፥ ከእግዚአብሔር ወልድ፡ ኢየሱስ መሲሕ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት በተቀበልናት፡ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን።

በሙታን ትንሣኤ፥ በዘለዓለምም ሕይወት እናምናለን። ለዘለዓለሙ፤አሜን።