ሰሙነ ሕማማት፥ ሥርዓተ ጸሎት፥ ሆሣዕና በአርያም፥ ሰው ሠራሽ ሥርዓት፥ የፋሲካ ራት፥ ምሥጢረ ቍርባን፥ ክህነት ሥርዓታት፥ ኅብስተ አኰቴት፥ ጽዋዓ በረከት፥ ጉልባን፥ በርባን፥ ሰፍነግ፥ ቅዳሜ ስዑር፥ መለኮታዊ ዐዋጅ፥ እብኖዲ፥ ታዖስ፥ ማስያስ፥ አማኑኤል፥ ትስቡጣ። መጋቢት ፳ ቀን፡ ፪ሺ፱ ዓ.ም. (29 March 2017).

የ፪ሺ፱ ዓመተ ምሕረት የሕማማት መልእክትና ሥርዓተ ጸሎት።

ፈጣሪያችንና አምላካችን ኢየሱስ መሲሕ፡ ምንጊዜም ከማትለየው፡ ከእግዝእተብሔር ቅድስት እናቱና እናታችን ድንግል ማርያም ጋር፡ አስቀድሞ፡ በዓለ-ኢትዮጵያን፥አከታትሎም፡ ተዝካረ-ኪዳነ ምሕረትንና ዓቢይ-ጾምን አስፈጽሞ፡ ለዘንድሮው በዓለ-ሆሣዕናና ዝክረ-ሰሙነ ሕማማት፡ እንኳን፡ በያለንበት፡ በደኅና አደረሰን!

ይድረስ፡- በምድርና በሰማያት በመላችው፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ዕቅፍ ውስጥ፡ የእግዚአብሔርና የኢትዮጵያ ልጆች፣ ነጋሢዎች፣ ካህናት ኾናችሁ “ኢትዮጵያ” በተባለችው አገር ሠፍራችሁ፥ በኪዳናዊው ኢትዮጵያዊ የጨውነት ህልውናችሁና የመብራትነት ተልእኳችሁም፡ አልጫና ጨለማ በኾነው፡ በዓለሙ ኹሉ አህጉራት፡ በመለኮታዊው ዕቅድ ተዘርታችሁና ተሠራጭታችሁ፣ ተልካችሁና ተመድባችሁ፡ በቀዳማዊቷ የትንሣኤና በዘለዓለማዊቷ የሰንበት ሕይወት ለምትኖሩ፡ ኪዳናውያት እኅቶችና ኪዳናውያን ወንድሞች!